ቀጥታ፡

አቃቤ ሕግ ሻለቃ ክንደያ ግርማይን ጨምሮ የቀድሞ የሜቴክ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ ክስ መሰረተ

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011 የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሻለቃ ክንደያ ግርማይን ጨምሮ በቀድሞ የሜቴክ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች  ላይ ክስ መሰረተ።

በዚህ የክስ መዝገብ ውስጥ የተጠቃለሉት የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ኢንዱስትሪ የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማት ኃላፊ የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ፣ ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ከበደ፣ ሻለቃ ፍፁም አጽበሃ፣ ሻለቃ ዋልታንጉሥ ተስፋው፣ ሻምበል ዊንታ በየነ፣ ሻለቃ ክንደያ ግርማይና አጠቃላይ አስመጪው አቶ ወልዳይ ገብረማርያም ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት የክስ መዝገቡን ለሻለቃ ክንደያ ግርማይ በንባብ ባሰማበት ጊዜ እንደጠቀሰው በአጠቃላይ ተከሳሾች በመንግሥት ላይ ከ71 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ነው ያለው ።

ተከሳሾቹ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ባለሦስት ፌዝ ተርሚናል ኮኔክተር ለማቅረብ የ98 ሚሊዮን 837 ሺህ 244 ብር ውል ፈጽመዋል፡፡

ነገር ግን ኃላፊዎቹ ከጠቅላላ አስመጪው አቶ ወልዳይ ገብረማርያም ጋር በጥቅም በመመሳጠር በ85 ሚሊዮን 783 ሺህ 318 ብር ለማቅረብ መስማማታቸውንም ጠቁሟል።

ኃላፊዎቹ ይኼንን ድርጊት የፈጸሙት የኮርፖሬሽኑን የግዥ መመሪያ በመተላለፍና ወጥቶ የነበረውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ባሸነፈው የውጭ ድርጅት ግዥ እንዳይፈጸም በማድረግ መሆኑንም የክስ መዝገቡ ይተነትናል።

ግዥውን በአግባቡ ለማካሄድም እ.ኤ.አ. የካቲት 14 ቀን 2016 በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ፣ 'ቲቢያ ድያንግ ኬብል ሊሚትድ' የሚባል የቻይና ኩባንያ በ12 ሚሊዮን 805 ሺህ 289 ብር ጨረታውን ያሸነፈ ቢሆንም፣ ኃላፊዎቹ ውድቅ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

በጨረታው መሠረት ኩባንያው ዕቃውን ገዝቶ እስከ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጎፋ መጋዘን ድረስ ለማጓጓዝ 14 ሚሊዮን 336 ሺህ 830 ብር ይፈጅ የነበረውን ውድቅ በማድረግና  በጥቅም በመመሳጠር በ85 ሚሊዮን 945 ሺህ 430 ብር ለነጋዴው ግለሰብ በመስጠት በመንግሥት ላይ የ71 ሚሊዮን 608 ሺህ 599 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል።

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ሻለቃ ክንደያ ግርማይ ከተከላካይ ጠበቃቸው ጋር በመመካከር የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡም ትእዛዝ ሰጥቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም