ስፖርት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንን አሰራር አደነቀ

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011 የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በመንግስት በጀት ብቻ ሳይወሰን ሌሎች አማራጮችንም በመጠቀም ስራዎችን በማከናወኑ አደነቀ።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን 17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ በኮሚሽኑ የማህበራት ማደረጃ ዳይሬከተር አቶ ሰለሞን ብርሃኑ ተገኝተው የፌዴሬሽኑን የስራ እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

ፌዴሬሽኑ የመንግስትን በጀት ብቻ ሳይጠብቅ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ስራዎችን ማከናወን መቻሉ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑንም በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል።

ለዚህም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ አቃቢ ንዋይና ሌሎች ስራ አስፈጻሚዎች አስተዋፆ ጉልህ መሆኑን የጠቀሱት  አቶ ሰለሞን ለሌሎች ፌዴሬሽኖችም አርአያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"የመንግስት በጀት ካልተለቀቀ በስተቀር ምንም አይነት ስራ ማከናወን አንችልም" ብለው ሚያስቡትም ጥሩ መንገድ የሚመራ መሆኑን ገልፀዋል።

የቦክስ ፌዴሬሽን አመራር አባላት ተግባብተውና  ተናበው በመስራት ያሳዩት አካሄድ ጥሩ ማሳያ መሆኑንም እንዲሁ።

የቦክስ ስፖርት አሁን ላይ በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ጥሩ የውጤት መሻሻል እየታየበት መሆኑም በጉባዓው ላይ ተመልክቷል።

ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ደረጃ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውም በማሳያነት ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ወሰን በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት በዘርፉ መሻሻሎች ቢታዩም ገና ብዙ መስራትን ይጠይቃል።

የቦክስ ስፖርት ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ የሚገኝበት ከመሆኑም በላይ በስፖርት ዲሲፕሊን የታነጹ ወጣቶችን ለማፍራትም ጉልህ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባባር እኤአ በ2020 የቶኪዮ ኦሎፒክ በመሳተፍ ውጤታማ ለመሆን ከወዲሁ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ በ1962 የተመሠረተ ሲሆን ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት በኦሊምፒክ መሣተፍ የጀመረችውም እ.ኤ.አ ከ1964 ቶክዮ ላይ በተደረገው ኦሊምፒክ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም