የሉሲ /ድንቅነሽ/ ቅሪተ አካል ሰመራ ሲገባ አቀባበል ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ /ድንቅነሽ/ ቅሪተ አካል ሰመራ ሲገባ አቀባበል ተደረገለት

ሰመራ የካቲት 15/2011 "ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር" በሚል ከአዲስ አበባ የተነሳው የሉሲ/ድንቅነሽ/ ቅሪተ አካል ዛሬ ጠዋት አፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሰመራ የደረሰው የሉሲ ቅሪተ አካል በብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት በሆኑት በሻለቃ ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ አመራር ሙፍቲ ሃጅ ኡመር ኢድሪስ መሪነት ነው፡፡
ከነዚሁ አባላት ጋር የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አህመድ አብዱቃድርና የቀድሞ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ እስማኤል አሊሴሮን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ይገኙበታል፡፡
የሉሲ ቅሪተ አካል ሰመራ ሲደርስ የክልሉ ፖሊስ ማርሽ ቡድን የተለያዩ ጣዕመ-ዜማዎችን በማሰማትና የአፋር ወጣቶችም ባህላዊ ጭፈራዎች ደማቅ ቀባበል ተደርጎላታል፡፡
በአቀባባሉ ስነስርዓት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሰመራ-ሎግያ አካባቢ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በቀጣይ ቅሪተ አካሉን በክልሉ የብሔር ብሔረሰቦች አዳራሽ በህዝብ እንደሚጎበኝ ፣ ስለሰላምና የህዝቦች አብሮነት እዲሁም ፍቅር የሚሰብኩ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ለዝግጅቱ ከወጣው ፕሮግራም ማወቅ ተችሏል፡፡
" ጉዞ ሉሲ ለሠላምና ለፍቅር” የሽኝት መርሃ ግብር ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሉሲ /ድንቅነሽ/ን ቅሪተ አካል ወደ መገኛዋ አፋር ክልል መሸኘቱ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ይህንን መርሃ ግብር ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር መሆኑ ታውቋል፡፡
በአፋር ክልል አዋሽ ሸለቆ ውስጥ በሚገኝ ሃዳር በተሰኘ አካባቢ የተገኘው የሉሲ ቅሪተ አካል ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ምድር መሆኗን አረጋግጧል።