ሲዳማ በና ድሬዳዋ ከነማን 3 ለ 1 አሸነፈ

83

ድሬዳዋ የካቲት 14/2011 ድሬዳዋ ከነማ ዛሬ በሜዳው ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸነፈ።

የሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ቡድናቸው አሁን ያለውን ጥንካሬ ጠብቆ ዋንጫውን ለመውሰድ እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ውድድር የመጨረሻ ጨዋታቸውን በዝናብ ታጅበው በድሬዳዋ ስታዲዮም ያካሄዱት ሁለቱ ቡድኖች ለመሸናነፍ ያሳዩት ፉክክር ተመልካቹን አዝናንቷል፡፡

በተለይ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ኢላማቸውን የጠበቁ ኳሶችን በመሞከር፣ በመከላከል ኳሷን ተቆጣጥሮ በመጫወት ሲዳማ ቡና ብልጫ ነበረው፡፡

በ8ተኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋው በረከት ሳሙኤል በራሱ ጎል ላይ በማስቆጠሩና  ሲዳማ 1 ለ 0 መምራቱ ይበልጥ ተጭኖ እንዲጫወት አስችሎታል፡፡ 

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ የመሸናነፍ ፉክክር ቢስተዋልም በሙሀል ሜዳው ብልጫ የነበረው ሲዳማ በ58ተኛ ደቂቃ በሀብታሙ ገዛኻኝ እና በ77ተኛው ደቂቃ በአዲስ ግደይ ጎሎችን አስቆጥሮ 3 ለ 0 ለመምራት ችሏል።

በ84ተኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከነማ ብቸኛውን ጎል በገናናው ረጋሳ አማካኝነት ቢያስቆጥርም ጨዋታው በሲዳማ 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ የሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ ዘርአይ "ሙሉ ሜዳው ያልተስተካከለ በመሆኑ የሚከብደን መስሎን ነበር፤ የመሀል ሜዳውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረን ማሸነፍ ችለናል" ብለዋል፡፡

ማሸነፋቸው አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት አሰልጣኙ "ነጥቡ ለዋንጫ የሚያደርጉትን ፉክክር ይበልጥ ለማጠናከር ያግዘናል" ብለዋል፡፡

‹‹ቡድኑ በወጣት የተገነባ ነው፤ በነዚህ ልጆች ላይ ትልቅ እምነት አለኝ፤ ለሁለተኛ ዙር ውድድር የምንፈልገውን ግብ እናሳካለን ›› ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አሰልጣኝ ስምኦን አባይ በበኩላቸው ሲዳማ ቡና ጠንካራ ቲም መሆኑን ተናግረው "ቡድኑ በአማራጭ ተጫዋች ስፋት ያለው በመሆኑ በመሀል ሜዳው ብልጫ ወስዶ አሸንፎናል" ብለዋል፡፡

በተጨማሪ የቡድናቸው የፊት አጥቂዎች በራስ መተማመን ማነስ ሣቢያ ያገኟቸውን ያለቁላቸው ጎል የሚሆኑ ኳሶች ማምከናቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ነው የገለፁት፡፡

በሁለተኛ ዙር ቡድን ያለበትን ክፍተቶች በመገምገም የተሸለ ውጤትና ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም አሰልጣኝ ስምኦን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም