አፍሪካ እና እንግሊዝ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

74

አዲስ አበባ የካቲት 14/2011 አፍሪካ እና እንግሊዝ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፈቂ መህመት እና የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ሃርየት ብላድዊን ናቸው።

ሁለቱ መሪዎች በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን በተለይም በታዳሽ ኃይል እና በናይጄሪያ አቢጃን ተካሄዶ በነበረው የአፍሪካ-አውሮፓ ህብረት ስብሰባ ላይ በጋራ ለመስራት ያቀዱትን ወደ ተግባር ለመለወጥ መክረዋል።

 እንግሊዝ ከአፍሪካ ጋር በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በመልካም አስተዳደር እና በስደተኞች ጉዳይ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ሚስ ሃርየት ተናግረዋል።

በዚህም በቀጣይ ሶስት ዓመታት ለአፍሪካ ልማት የሚውል 30 ሚሊዮን ፓውንድ የመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ገልፀው እንግሊዝ በ2020 ከቡድን 7 አባል አገራት የአፍሪካ ቀዳሚ አጋር የመሆን ትልም እንዳላት አብራርተዋል።

በተጨማሪም እንግሊዝ በአፍሪካ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ የማስፋትና በአፍሪካ ህብረትም የእንግሊዝ ተወካይ ከፍተኛ ባለሥልጣን የመመደብ ፍላጎት እንዳላትም እንዲሁ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፈቂ መህመት በበኩላቸው፤ አፍሪካ ከእንግሊዝ ጋር በትብብር መስራት እንደምትሻ ገልፀዋል።

አገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላትን የካበተ ልምድና አቅም ለአፍሪካ ለማካፈል የምታደርገውን ጥረት አድንቀው አፍሪካም በተለያዩ መስኮች ከእንግሊዝ ጋር የመስራት ፍላጎት አላት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም