''የአፋር ክልል ከቱሪዝም ሃብቱ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ነው''-ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
''የአፋር ክልል ከቱሪዝም ሃብቱ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ነው''-ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ
ሰመራ የካቲት 14/2011 የአፋር ክልል ከቱሪዝም ሃብቱ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስታወቁ።
በአፍሮጽዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ሪዞርት በሰመራ ከተማ በይፋ ተመርቋል።
ርዕሰ-መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ክልሉ በቱሪዝም መስክ መዋለ ነዋያቸውን ከሚያፈሱ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ሀብቱን በተገቢው መልክ ለዓለም ኅብረተሰብ ለማስተዋወቅ ተጠቃሚ ለመሆን ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ባለመኖሩ ሲቸገር እንደነበረ አስታውሰዋል።
ሪዞርቱ ክልሉን ከቱሪዝም ሀብቱ ብቻ ሳይሆን፤ አገር አቀፍ ስብሰባዎችንና መድረኮች ለማስተናገድ እንደሚቃልለው ርዕሰ መስተዳደሩ ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ከግል ባለሃብቱና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ደረጃ ችግሩን እየፈታ መሆኑን አተናግረዋል።
የሪዞርቱ ባለቤት የሆኑት የአፋሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት አቶ ሲሳይ ደስታ ሪዞርቱ በአምስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፉ አራት ፕሬዚዳንታዊ ቪላዎችን ጨምሮ 144 ደረጃውን የጠበቁ መኝታ ቤቶች አሉት።
የሪዞርቱን ግንባታ ለማጠናቀቅም 22 ወራት ፈጅቷል ብለዋል።
ሪዞርቱ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር 400ሰዎች ሥራ እንደሚፈጥር በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
የኩሪፍቱ ሪዞርቶች ሆቴል ባለቤት አቶ ታዲዎስ ጌታቸው አንደተናገሩት ሪዞርቱ በክልሉ በቂ የቱሪስቶች ፍሰት አንዲኖር በማድረግና የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ያዕቆብ መካሉ ክልሉ ያሉትን የቱሪስት መስህቦች ለማልማት የቱሪስቶች ማረፊያዎች መገንባታቸው ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ማህበራቸው ከዘርፉ ተገቢው ጥቅም አንዲገኝ ድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
ክልሉ ሉሲን ጨምሮ የጥንታዊ ሰው ቅሪተ-አካል መገኛ ቦታዎች፣የኤርታአሌ እሳተጎሞራ አንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገርም ዳሎል ፖታሽም የቱሪስት መስህቦቹ ናቸው።
የበርካታ የተፈጥሮ ፍል ውሃዎችም ባለቤትም ነው።