ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር ዛሬ በይፋ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር ዛሬ በይፋ ተጀመረ
አዲስአበባ የካቲት 14/2011 "ጉዞ ሉሲ ለሠላምና ለፍቅር'' የተሰኘው ፕሮጀክት ዛሬ የሉሲን ቅሪተ አካል ወደ አፋር በመሸኘት ተጀምሯል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያውያን የአንድ የሉሲ ልጆች መሆናቸውን በማሳወቅ በአገሪቱ ሰላምና ፍቅር እንዲነግስ የማድረግ ዓላማን ያነገበ ነው።
“የሚያምርብን ፍቅርና አብሮነታችን ነው”
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ
ሽኝቱ የተከናወነው ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደ ስነ-ስርዓት ነው።
በዚሁ ወቅት ሰላም አንድነትንና ፍቅርን የማጠናከር ተልዕኮ ያነገበው ጉዞ ሉሲ ፕሮጀክት እንዲሳካ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ተብሏል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ባደረጉት ንግግር "የሚያምርብን ፍቅርና አብሮነታችን ነው" የሚለው የጉዞው መሪ ቃል ግዙፍ አገራዊ አገራዊ ኃሳብ ይዟል ብለዋል።
መልእክቱ "ኢትዮጵያዊያን የተሳሰሩና በታሪክ የተቆራኙ" መሆናችንን ያስታውሰናል ሲሉም ተናግረዋል።
በተጓዳኝም በታሪክና በሃይማኖት ተቀባይነት የሌላቸው የአገሪቱን ሠላም የሚፈታተኑ አመለካከቶችን ለማስወገድ ጉዞው ዓይነተኛ መሳሪያ እንደሆነም አፈ ጉባኤው ገልፀዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት "ወደአያቶቼ አገር መጣሁ" በማለት መናገራቸውን ያስታወሱት አፈ-ጉባኤው ኢትዮጵያዊያን በሉሲ አማካኝነት ከሌሎች ሃገራት ህዝቦች ጋር ያላቸውን ዝምድና ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳሁን "ሉሲ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከዓለም ጋር የምታስተሳስር ገመድ ነች" ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም በጉዞው ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ እንዳይለያዩ ያስተሳሰሯቸው ባህላዊ እሴትና ቅርሶችም ሉሲን አጅበው ይጓዛሉ ሲሉ ገልፀዋል።
"ሉሲ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከዓለም ጋር የምታስተሳስር ገመድ ነች"
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳሁን
ይህ ጉዞ ልጆቻችን ያስተሳሰሩንን ገመዶች እንዲረዱ የሚያስችል በመሆኑ በተለይ ወላጆች ይሄንን በደንብ ተረድተው ለልጆች ማስተላለፍ እንዲችሉ የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሚሆንም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ የተቀየሰው "ኢትዮጵያውያን ተነጣጥለን ስራ የማንሰራ ተነጣጥለን መኖር የማንችል መሆናችንንም ለማሳየት ነው" ብለዋል።
"በጋራ የሚሰሩ ስራዎች ውጤት ላይ ይደርሳሉ፤ በጋራ መኖርም ውጤት ላይ ያደርሳል ከሰላም ያለፈ እድገትን ያመጣል" በማለት ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ለሰላም፣ አንድነትና ፍቅር መጠናከር የያዘውን ተልዕኮ እንዲወጣ ሁሉም እንዲረባረብም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያዊነት ቅዱስ መንፈስ፣ ኩራትና ጀግንነት እንዲሁም ክብር መሆኑን ለልጆቻችንን እናስተላልፍ ሲሉ ተናግረዋል።
በዛሬው እለት የተሸኘችው ሉሲ በመላው አገሪቱ በመዘዋወር ስለሰላም እና ፍቅር የያዘቸውን መልእክት የምታደርስ ሲሆን የመጀመሪያ ጉዞዋንም መገኛዋ በሆነችው አፋር ክልል ትጀምራለች።
የሉሲ ቅሪተ አካል በየክልሉ ለአምስት ቀናት ይቆያለች ተብሏል።
ጉዞ ሉሲን በመተባበር ያዘጋጁት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ናቸው።
በኢትዮጵያ አፋር ምድር በ1967 ዓም የተገኘችው ሉሲ ቅሪት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ እንዳለው የሚነገር ሲሆን ይህም አስካሁን በምርምር በመጀመሪያ ከተገኙት የሰው ዘር ቅሪቶች ረዥም እድሜ ተብሎ ይወሰዳል።
ከዚህም ሌላ 40 በመቶ የሚሆነውን ትክክለኛ የሰውነት አካል በመያዝ ለቅድመ የሰው ዘር የቀረበ ፍንጭ የሰጠች በመሆኗም ሉሲ ዓለም አቀፍ ዝናዋ ከፍተኛ ነው።