ኢትዮጵያና ኡራጋይ የፖለቲካ ምክክር ስምምነት ተፈራረሙ

72

አዲስ አበባ  የካቲት 14/2011ኢትዮጵያና ኡራጋይ የፖለቲካ ምክክር ስምምነት ተፈራረሙ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የኡራጋይ አቻቸውን ሮዶልፎ ኒን ኖቫዎን በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በአገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች የመከሩ ሲሆን ልምድ መለዋወጥና መደጋገፍ የሚያስችላቸውን የፖለቲካ ምክክር ስምምነት ተፈራርመዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ስምምነቱ አገራቱ ቋሚ የግንኙነት ጊዜ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ የጋራ አቋማቸው ላይ ተደጋግፈው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም ተስማምተዋል ብለዋል።

ባለስልጣናቱ ኡራጋይ የዳበረ ልምድ ያካበተችበትን የከብት እርባታ ልምድ ለኢትዮጵያ በምታካፍልበት ሁኔታም ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ በላቲን አሜሪካ ያሏት ኤምባሲዎች ውስን በመሆናቸው በብራዚል የሚገኘው ኤምባሲ የኡራጋይን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተልዕኮ እንዲሰራ ሃላፊነት ተሰጥቶታል።

ኡራጋይ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2016 ጀምራ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከፍታ እየሰራች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም