የአንበሳ ግቢ መዝናኛ ማዕከል ስራ ቢጀምርም የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
የአንበሳ ግቢ መዝናኛ ማዕከል ስራ ቢጀምርም የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም
የካቲት 14 /2011 በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው በ28 ሚሊዮን ብር እድሳት የተደረገለት የአንበሳ ግቢ መዝናኛ ማዕከል የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑ ተገልጿል።
የከተማዋ ኮንስትራክሽን ቢሮ በበኩሉ የማዕከሉ እድሳት ቀሪ ሥራዎች በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ይጠናቀቃል ብሏል።
በአዲስ ዙ ፓርክ የአንበሳ ግቢ መዝናኛ ማዕከል በዘመናዊ መንገድ ተገንብቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ከሁለት ዓመት በፊት ተዘግቶ ግንባታው ሲከናውን ቆይቷል፡፡
ይሁንና ሰሞኑን ስራውን የጀመረው ማዕከሉ አንዳንድ ግንባታዎች በወቅቱ ባለመጠቀቃቸው ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ሊሰጥ አልቻለም።
በአንበሳ ግቢ መዝናኛ ማዕከል በጉብኝት ላይ ካገኘናቸው መካከል አቶ ይበልጣል ከማል፤ ለመዝናኛ አገልግሎት የተሰሩ ካፌዎችም ሆኑ መፀዳጃ ቤቶች በአግባቡ ስራ አለመጀመራቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸው፤ ፓርኩ ስራ መጀመሩ ጥሩ ቢሆንም በተሟላ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
ማእከሉ ተጨማሪ እንስሶችን ወደ ግቢው በማስገባት አሁን ከሚሰጠው አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ሊንቀሳቀስ ይገባል ያለችው ወ/ሪት መሰረት ለማ፤ የእድሳት ሥራው ይሄን ያህል ጊዜ ቆይቶ በተሟላ ሁኔታ ስራውን አለመጀመሩ ትክክል አይደለም ብላለች።
የአንበሳ ግቢ መዝናኛ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ይርጋለም አያሌው ስለሁኔታው ተጠይቀው ከሁለት ዓመት በፊት 28 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ እድሳቱ መጀመሩን ጠቁመው እድሳቱ ለረጂም ግዜ በመቆየቱ በህብረተሰቡ ቅሬታን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
የተለያዩ ኮንትራክተሮች ተቀያይረውበት በቅርቡ ስራ እንዲጀምር የተደረገው ፓርኩ፤ የህዝብ መፀዳጃ ቤቱን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ግንባታቸው ባለመጠናቀቁ አገልግሎቱን በተሟላ መንገድ ለማስጀመር አለመቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በግንባታው ሂደት እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ቢያሳውቁም እስካሁን ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉም ነው አቶ ይርጋለም ያብራሩት፡፡
የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው የማዕከሉ አብዛኞቹ ግንባታዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረው፤ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የዲዛይን ለውጦች መደረጋቸው የግንባታው ጊዜ እንዲራዘም አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
ህብረተሰቡ ቅሬታ ካነሳባቸው አገልግሎት መስጫዎች መካከልም የህዝብ መፀዳጃ ቤት ተጠናቆ ርክክብ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
ማእከሉ ከኮንስትራክሽን እውቅና ውጭ ያሰራው ዲዛይን አንዳንዶቹ አስፈላጊ ባለመሆናቸው ውድቅ ተደርገዋል ያሉት ኢንጅነር ዮናስ፤ “እድሜ ጠገብ ዛፎች እየተቆረጡ ግንባታ ማካሄድ ለፓርኩ ተገቢ አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዲዛይኖችን በማሻሻል ዛፎች ሳይቆረጡ አምስት ያህል አዳዲስ የእንስሳ ማቆያ ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውንም ነው እንጂነር ዮናስ ጨምረው የገለጹት፡፡
በቀሪ ሁለት ሳምንታት የቀሩ ጥቃቅን ስራዎች ተጠናቀው ፓርኩ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ይጀምራልም ብለዋል።
በአንበሳ ግቢ መዝናና ማዕከል በአሁኑ ወቅት አስር አንበሶች፣ አንድ አምባራይሌ፣ አንድ ሚዳቋ፣ አንድ የባሌ ጦጣ ፣ አንድ ጭላዳ ዥንጀሮ ና የተለያዩ አእዋፋት እንደሚገኙ ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡