ቀጥታ፡

በአካባቢያቸው የመሰረት ልማት አውታሮች ባለመሟላታቸው መቸገራቸውን የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

ፍቼ  የካቲት 14/2011 በፍቼ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች የመሰረት ልማት አውታሮች ባለመሟላታቸው መቸገራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማዋ የቀበሌ 01፣ 02፣ 03 እና 04 ቀበሌ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት መኖሪያ ቤት ሰርተው መኖር ከጀመሩ 11 ዓመታትን ቢያስቆጥሩም እስካሁን ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመጠጥ ውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ተቸግረዋል።

የቀበሌ ዐ3 ነዋሪ አቶ ታደሰ አጋ እንዳሉት በአካባቢያቸው የቧንቧ ውሃ መስመር ባለመዘርጋቱ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት አልቻሉም።

በዚህ ምክንያት ንጽህናው ያልተጠበቀ የወንዝ ውሃን ለመጠጥነት ለመጠቀም በመገደዳቸው እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው በተደጋጋሚ ለውሃ ወለድ በሽታ እየተጋለጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀበሌያቸው የኤሌትሪክ መስመር ባለመዘርጋቱ ነዋሪዎች ከተጐራባች ቀበሌዎች ከግለሰቦች ላይ በህገ ወጥ መንገድ በመጥለፍ ለመጠቀም መገደዳቸውን የገለጹት ደግሞ የቀበሌ ዐ4 ነዋሪዎች ተወካይ አቶ ካሱ መርዳሳ ናቸው።

"የኤሌክትሪክ መስመሩን የሚያጋሩ ግለሰቦች ለአገልግሎቱ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቁም ለብዝበዛ ተዳርገናል" ብለዋል።

የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለመሰራታቸውም ነዋሪው ወጥቶ ለመግባትም ሆነ የታክሲ አገልግሎት ለማግኘት እንዳልቻሉ አመልክተዋል።

አቶ ካሱ እንዳሉት በአካባቢያቸው የሚስተዋለው የመሰረተ ልማት ችግር እንዲፈታ ነዋሪው 180 ሺህ ብር ቢያዋጣም የከተማዋ መስተዳድር ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለማድረጉ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም።

በህጋዊ መንገድ ተመርተው ለገነቡት መኖሪያ ቤት የውሃ፣ የመብራትና የመንገድ መሰረተ ልማት አውታሮች ባለመዘርጋታቸው በተለይ እናቶችና ህፃናት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ በከተማው የቀበሌ ዐ1 ነዋሪ ወይዘሮ ተሰሜ ዋቅቶላ ናቸው።

የከተማው አስተዳደር ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለይቶ እልባት እንዲሰጥ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

የፍቼ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሁንዴ ከበደ በተጠቀሱት ቀበሌዎች የጐላ የመሰረተ ልማት ችግር መኖሩን አምነው ከነዋሪዎቹ ጋር ወጪን በመጋራት ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

"አዲስ የተዋቀረው የከተማዋ ካቢኔ ለአካባቢዎቹ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው" ያሉት ከንቲባው በቅርቡ የጨረታ ሂደት ተጠናቆ የ33 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ችግሩን ለማቃለልም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍቼ ዲስትሪክት 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ክፍያ በመፈፀሙ በቅርቡ የኤሌክትርክ ኃይል መስመር ዝርጋታ ሥራው እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በቀጣይ በሚሰሩ ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየትና የጋራ ለማድረግ የከተማው አስተዳደር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፍቼ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲሳ ጫላ የከተማው ማዘጋጃ ቤት በፈጸመው ውል መሰረት ለዋና ዋና መንገዶች የመስመር ዝርጋታና የትራንስፎርመር ተከላ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህም የጥቂት ነዋሪዎችን ችግር ብቻ የሚያቃልል መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዲሳ የነዋሪዎቹ ፍላጐት ግን ከ1 ሺህ 6ዐዐ በላይ ቆጣሪ የሚፈልግ በመሆኑ ሊጣጣም እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ምሰሶዎችና ትራንስፎርመሮችን ከሟሟላት ጀምሮ የኃይል ፍጆታዎችን የሚያቃልሉ ሥራዎችን ዲስትሪክቱ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም