የአፋር ክልል መንግሥት ሉሲን ለመቀበል ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልል መንግሥት ሉሲን ለመቀበል ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ አለ
ሰመራ የካቲት 14/2011 የአፋር ክልል መንግሥት ወደ ተገኘችበት ሥፍራ የምትመጣዋን ሉሲን ለመቀበል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
''ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር!'' በሚል መርሐ-ግብር በሰመራ በሚካሄድ ዝግጅት ውይይት፣ ጥናታዊ ጽሁፎችና የኪነጥበብ ሥራዎች ይቀርባሉ።
ኃላፊው አቶ ዓሊ መሐመድ እንደተናገሩት ሉሲ የሰው ዘር መገኛ ወደሆነችበት ምድሯ መመለሷ የክልሉን የቱሪዝም ሃብት ለማስተዋወቅና የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ያነቃቃዋል።
በተጨማሪም የሰው ልጆች አንድነትን ስለምታሳይ ከቱሪስት መስህብነት ባሻገር አብሮነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ለአቀባበሉ የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናትና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ኮሚቴ መቋቋሙንና በአቀባበሉ ላይም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ባህላዊ የጎሳ መሪዎች ይሳተፋሉ።
እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶች ባህላዊ ጭፈራዎችንና ትርዒቶችን በማሳየት ከሱልጣን ዓሊ ሚራህ አየር ማረፊያ ጀምሮ አቀባበል እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ሉሲ ለአንድ ሳምንት በሰመራ ከተማ በሚኖራት ቆይታ በከተማዋ ነዋሪዎች እንደምትጎበኝም አቶ ዓሊ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ምሁራን አንድነትና ፍቅርን የሚያስተምሩበት ሲምፖዚዬም የሚስተናገድ ሲሆን፣የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ያቀርባሉ።
የሰመራ ከተማ ነዋሪ አቶ መሐመድ አህመድ በሰጡት አስተያየት ሉሲ ወደ ክልሉ መምጣቷ በክልሉ ያለውን ሰላም፤ አብሮነትና ተቻችሎ በጋራ የመኖር ባህልን ለመጠበቅ መነቃቃት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ሌላው የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰዲቅ ሁሴን በበኩሉ የሉሲ መምጣት ወጣቱ የሕዝቦች አብሮነትና አንድነት እንዲሁም በሰላም እሴት ግንባታ ከአባቶች ጋር የሚመካከርበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
''ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር!''በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አስተባባሪነት የባህልና ቱሪዝምና የሰላም ሚኒስቴሮች ያዘጋጁት መርሐ ግብር ነው።