ቀጥታ፡

በብሔራዊ ፓርኩ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከል እንደሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ

ጎባ የካቲት 13/2011 በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሚገኙ ብዝሃ ሕይወት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንደሚሰሩ ገለጹ፡፡

ፓርኩን ከችግር ለማውጣት ከተለያዩ አካላት ጋር ሰሞኑን በባሌ ጎባ የባለድርሻ አካላት የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል፡፡  

በፓርኩ ብዝሃ ሕይወት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በመከላከል ፓርኩን የጎብኚዎች መዳረሻ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የፓርኩን ህልውና ጭምር እየተፈታታኑ የሚገኙት የልቅ ግጦሽና ህገ ወጥ ሰፈራ የመንግስት አካላት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የሚፈልጉ ቁልፍ ችግሮች ሆነው ተለይቷል፡፡

ፓርኩ አያሌ የእንስሳትና የእጽዋት ብዝሃ ህይወት ያቀፈ እንደመሆኑ ከገጠሙት ችግሮች በመታደግ የክልሉን ብሎም የአገሪቱን የኢኮቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ተናግረዋል፡፡

የዞኑ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደበላ ከበደ እንደተናገሩት ፓርኩን ከችግሮቹ ለማውጣት በቅንጅት መሰራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በዞኑ የሚታየው የደን ጭፍጨፋ ለዱር እንስሳትም ሆነ ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር እየፈጠረ ያለውን ችግር ለመፍታት እስከ ቀበሌ ደረጃ በተዋቀረው አደረጃጀት በመጠቀም ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ፡፡

የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱርዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው "ቢሮው ፓርኩን ከችግር ለመታደግና የቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በግንባር ቀደምትነት ይሰራል" ብለዋል፡፡

በፓርኩ ላይ እየደረሱየሚገኙትን ሰው ሰራሽ ችግሮችን መፍታት ፓርኩ ለቱርዝም ኢንዱስትሪው ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ፓርኩን በዓለም ቅርስነት በቋሚነት ለማስመዝገብ የሚደረገውንም ጥረት እንደሚያግዝ አመልክተዋል፡፡

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በመረዳት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው አቶ ከበደ የገለጹት፡፡

"የደን ጭፍጨፋን ለመከላከልና የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ መንግስትና በዘርፉ የተሰማሩ ግብረ ስናይ ድርጅቶች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ቅድሚያ ሰጥተው ከሰሩ ለውጥ ይመጣል" ያሉት ደግሞ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደውድ አብዱሪ ናቸው፡፡  

የፍራንክፈርት ዞሎጂካል ሶሳይት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሁሴን ኢድሪስ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በፓርኩ አካባቢ በሚኖሩ የማህበረሰብ አካላት ላይ የተሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትግባራት ውጤት እያስገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ማህበረሰቡ ከፓርኩ ወሰን ውጪ በሌሎች የሥራ መስኮች በመሰመራት ህይወቱን እንዲለውጥ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ከተሰራበት በፓርኩ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ትርጉም ባለው መልኩ ሊቀንሰው እንደሚችል እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሁሴን እንዳሉት ድርጅታቸው በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት አካላት ጋር በመቀነጀት ፓርኩን ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት በቀጣይነትም እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀጂ በበኩላቸው የሀገር ሀብት በሆነው የባሌ ተራሮች ፓርክ ላይ የተጋረጠውን ሰው ሰራሽ አደጋ ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮቹን በመጠቀም ህገ ወጥ ሰፈራ፤ የደን ጭፍጨፋና ህገ ወጥ የእንስሳት አደንን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የፓርኩን ህልውና ለመጠበቅ የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ናቸው፡፡

"ልቅ ግጦሽና ህገወጥ ሰፈራን ጨምሮ የፓርኩን ህልውና እየተፈታተኑ የሚገኙ ተግዳሮቶችን መፍታት ፓርኩን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ያቀላጥፋል" ብለዋል፡፡

የፓርኩን ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንዲፈቱ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላትና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲረባረቡም ጠይቀዋል፡፡ 

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ጊዜያዊ መዝገብ ላይ የሰፈረው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደጋ አጋዘንና ቀይ ቀበሮን ጨምሮ የብዙ አእወፋትና እጽዋት ብዝሃህይወት መገኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም