ባንኮች በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና እንዲያበድሩ የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባንኮች በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና እንዲያበድሩ የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 13/2011 ተንቀሳቃሽ ንብረት በዋስትና በመያዝ ባንኮች ብድር ሊሰጡ የሚችሉበት አዲስ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ቋሚም ሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት የሌላቸው የአዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን በዋስትና በማስያዝ ብድር የሚያገኙበት አሰራር እንደሚዘረጋም ተጠቁሟል።
ባንኩ እየሰራው ያለው ይህ የማሻሻያ አዋጅ በቋሚ ንብረት እጦት የሚያሲዙት አጥተው ያሰቡትን ለመስራት ያልቻሉ ዜጎችን ችግር ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተጠቆመው።
የባንኩ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ እንደተናገሩት፤ ተንቀሳቃሽ ንብረትን ይዘው ባንኮች ብድር ሊሰጡ የሚችሉበት አዲስ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ታስቧል።
አሰራሩ ለኢትዮጵያ አዲስ ቢሆንም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ባንኮች ቋሚ ንብረትን ብቻ ይዘው ብድር የሚሰጡ በመሆናቸው ቋሚ ንብረት የሌላቸው የብድር አገልግሎት የማግኘት እድላቸው አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
''አብዛኛው ዜጋ ቋሚ ንብረት ለማስያዝ ባለመቻሉ ኢኮኖሚው ላይ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ እንዲሆን በማድረጉ ይህ አዲስ መመሪያ እንዲዘጋጅ ምክንያት ሆኗል'' ብለዋል።
የብድር አሰጣጡን በሚመለከት አዋጆችና ደንቦች እየተዘጋጁ ሲሆን የብድር አሰራሩም በነዚህ ህጎች መሰረት ተፈፃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
ከዚያም ባለፈ ቋሚም ሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት የሌላቸው ግን አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎችም የፈጠራ ሃሳባቸውን በዋስትና በማስያዝ ብድር የሚያገኙበት አሰራር እንደሚዘረጋ የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶክተር ይናገር ደሴ ተናግረዋል።
በዚህ ማሻሻያ አዋጅ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ባንኩ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት የሪፎርም ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ዶክተር ይናገር በነዚህ ጊዜያቶች የማያሰሩ 10 መመሪያዎችን ከመሻር ባለፈ 3 ረቂቅ አዋጆችን ለማስፀደቅ ብሔራዊ ባንኩ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።