ቀጥታ፡

በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መቸገራቸውን የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ

ዲላ የካቲት 13/2011 በተደጋጋሚ በሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መቸገራቸውን የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲላ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በበኩሉ ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት በከተማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የቆየ ችግር ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ ነው፡፡

ይህም ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የተገናኙ የንግድና ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን እንቅፋት እየፈጠረ በመሆኑ መቸገራቸውን ነው የገለጹት ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አዲስ አየለ እንዳሉት ሳይፈታ የቆየው የዲላ ከተማ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ሰሞኑን ተባብሶ በተደጋጋሚ እየተቆራረጠባቸው ነው ፡፡

በቀን ከአራት ጊዜ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚቋረጥና ሳይመለስ ከሁለት ሰዓት በላይ እንደሚቆይም አመልክተዋል።

በማስታወቂያና ህትመት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን የገለጹት አቶ አዲስ፣ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ማግኘት ያለባቸውን ገቢ እየቀነሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

" በዲላ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በየቀኑ ለተደጋጋሚ ጊዜ ከመጥፋት ባሻገር ሳይመጣ በዚያው የሚያድርበት አጋጣሚ አለ" ያሉት ደግሞ አቶ አለማየሁ ኤጄርሳ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

ሥራቸው ከጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ውሃን በሞተር ኃይል መሳብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተደጋግሞ እየጠፋ የሚመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል   የየዕለት ተግባራቸውን ፈታኝ እንዳደረገብቸው ተናግረዋል ፡፡

አቶ ጌታቸው ገብረሚካኤል የተባሉ ሌላው ነዋሪ ደግሞ ሰሞኑን በከተማዋ በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ ያለው የኃይል እቅርቦት ቴሌቪዥንና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎቻቸውን ለብልሽት እንደዳረገባቸው አስረድተዋል ፡፡

ችግሩ በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲላ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀን ገረመው በከተማዋ የሚታየውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ አምነው ለችግሩ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

ከነዚህ ምክንያቶች ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ማርጀት መሆኑን ጠቅሰው በእዚህም መስመሮቹ በቀላሉ ለጉዳት የሚጋለጡበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዲላና አካባቢው ያሉ የኤሌክትሪክ መስመሮች በአብዛኛው በዛፎች መሀል የሚያልፉ መሆናቸውና ዛፎቹ በሰዎችም ሆነ በነፋስ ኃይል በሚወድቁበት ጊዜ የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት ተናግረዋል ፡፡

በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ጥናት መደረጉን የገለጹት አቶ ደጀን ያረጁ ምሰሶዎቹንና የኤሌክትሪክ መስመሮችን በአዲስ መስመር ለመተካት በተቋም ደረጃ እቅድ መያዙን ተናግረዋል ፡፡

ማዕከሉ ያለውን ውስን የሰው ኃይልና አቅም በመጠቀም የማስተካከያ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ለእዚህም  ከመስመሮች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዛፎች የመመንጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በከተማ ውስጥ የሚተከሉ ዛፎችና ሌሎች ዕጽዋት ከኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር እንዳይገናኙ ለማድረግ ከነዋሪዎች ጋር የተለያዩ መድረኮችን በመካሄድ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እነዚህንና መሰል ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቋርጦ የሚቆይባቸውን ጊዜያት ለማሳጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከከተማ ውጭ ካሉ ቀበሌዎች አመራሮች ጋርም ተቀራርቦ ለመስራት ግንኙነት እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም