የድንቅነሽ ድንቅ ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
የድንቅነሽ ድንቅ ጉዞ
የሺመቤት ደመቀ /ኢዜአ/
ሳር እና አልፎ አልፎ ዛፎች የሚታዩበት ወንዝ ዳርቻ፤ ሴቲቷ ጎርደድ ጎርደድ እያለች የመኖሪያ አካባቢዋን እየቃኘች ሳለ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለላት ውብና ለሙን መንደሯን ረዘም ያለው ዛፍ ላይ ወጥታ ቁልቁል መመልከት፤ አደረገችውም።
በግምት ከ12 ሜትር በሚረዝመው ትልቅ ዛፍ ላይ ወጣችና በተፈጥሮ ልምላሜ የታደለውን ቀዬዋን ፣ የልጅ ልጆቿን ቡረቃ ቁልቁል እየተመለከተች ተመሰጠች ፤ በዚያው እንቅልፍ ሸለብ አደረጋት ፣ ንጹሁን አየር እየሳበች ሰመመን ውስጥ ገባች ፤ የወፎች ዝማሬ፣ የወንዙ ሿሿታ፣ የልጆች ጨዋታና ጫጫታ ድምጽ እየራቋት እየራቋት ጭልጥ ብላ ነጎደች።
ጎልማሳዋ ሴት በእንቅልፍ ዓለሟ ደልዳላው መኝታዋ ላይ ያለች መሰላትና ልትመቻች ገልበጥ አለች በዚያው ቅፅበትም እጆቿ ጨብጠውት የነበረውን የዛፉን ቅርንጫፎች ለቀቁና ዥውውው … ብላ ቁልቁል ወደ መሬት ወደቀች፤ ከጣፋጩ እንቅልፏ አልነቃችም እስከ ወዲያኛው አሸለበች፤ የምድረ-አፋር ሀዳር መንደር ነዋሪዋ እማማ ሉሲ /ድንቅነሽ/።
"የሉሲ ጉዞ ከኢትዮጵያ ባለፈ በአፍሪካ አገሮች የሚካሄድ ሲሆን በተለይ አፍሪካዊያን ከሉሲ የዘር ሀረግ መመዘዛቸውን ተረድተው ኅብረታቸውን እንዲያጠናክሩ የማነሳሳት ዓላማም አለው።"
የሰው ልጆችን አመጣጥ ለማወቅ የሚደረገውን ምርምር በማገዝ ረገድ እስካሁን ወደር ስላልተገኘላት ሉሲ አሟሟት የተካሄደውን የጥናት ውጤት ሳነብ ምናቤ ስለ አሟሟቷ የሳለው ነው። ድንቅነሽ ወደ መንደሯ ብሎም ወደ መገኛ አገሯ ኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ልትጓዝ የመሆኑን ወሬ ስሰማ ነው በዚህ ወቅት እርሷን ማንሳቴ። ሉሲ ከሐምሌ 29 ቀን 1999 እስከ ሚያዝያ 23 ቀን 2005 ዓ.ም በአሜሪካ ቆይታ ማድረጓን፣ በሚሊዮን በሚቆጠሩ የአገሪቱ ነዋሪዎችና ቱሪስቶች መጎብኝቷንና በዚህም ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቷን ልብ ይሏል።
ጊዜው ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም። ስፍራው የስምጥ ሸለቆው አፋር ምድር ሀዳር፤ ዶናልድ ጆንሰንና ቶም ግሬይ የተባሉ አሜሪካዊያን ሳይንቲስቶች በሳይንሳዊ ስሟ ‘አውስትራሎፒተከስ አፋራንሲስ’ የተሰኘችውን የሉሲን ቅሪተ አካል አገኙ። ግኝቱ የፈጠረባቸውን ደስታ በድንኳናቸው ውስጥ ሆነው በፌሽታ አከበሩት። በዘመኑ ዝነኞች የነበሩት ዘ ቢትልስ /አሜሪካዊያን ድምጻዊያን/ “Lucy in the Sky with Diamonds” ዜማ የፌሽታው ማድመቂያ ነበር፤ እናም ‘ሉሲ’ የአዲሷ ቅሪተ-አካል መጠሪያ ሆነ።
እማማ ሉሲ /ድንቅነሽ/ "ጉዞ ሉሲ ለሠላምና ለፍቅር" በተሰኘ መርሃ-ግብር ከቀዬዋ ባሻገር ወደ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን ኬንያና ኡጋንዳ እንደምትጓዝ ሰማን። በጉዞው የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የፍቅርና የሠላም መልዕክቶች ይተላለፋሉ። የሉሲ ጉዞ ከኢትዮጵያ ባለፈ በአፍሪካ አገሮች የሚካሄድ ሲሆን በተለይ አፍሪካዊያን ከሉሲ የዘር ሀረግ መመዘዛቸውን ተረድተው ኅብረታቸውን እንዲያጠናክሩ የማነሳሳት ዓላማም አለው።
"ሃይማኖትም ይሁን ሳይንስ የሰው ዘር መገኛ አንድ መሆኑን እንጂ በየብሔሩ ልዩነት መኖሩን አይነግሩንም። መነሻችን ሳይንሱ ነውና ሳይንሱ እንደሚለው ሉሲ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳትሆን የሰው ልጆችም እናት ናት።"
ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ማስቆጠሩ በሚነገርለት የሉሲ ቅሪተ-አካል የተደረገ ጥናት ድንቅነሽ በጎልማሳነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረች፣ ከዘመናዊው ሰው ጋርም በእጅጉ ተቀራራቢ የሆነችና መራመድም ትችል እንደነበር ያሳያል። ከቅሪተ-አካሏ በመነሳት ስለ ሰው ልጆች እንቅስቃሴ መናገር እንደተቻለም ይነገራል።
የቅሪተ-አካል ተመራማሪው ዶክተር ሮበርት ብሉመንሻይ “በሉሲ ቅሪተ አካል የተገኙት የራስ ቅልና ጥርስ ስለ ሉሲ አመጋገብና ስለ አንጎሏ መጠን ለማወቅ ያስቻሉን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው ይላሉ። ቀሪ የአጥንት ክፍሎቿም ሉሲ በሁለት እግሮቿ ትራመድ እንደነበር ወሳኝ መረጃ የሰጡን ናቸው።" ብለዋል። ሉሲ እንደ ሰው ልጆች ትራመድ ነበር የሚል ግምት ቢኖርም ከጦጣዎች የምትጋራው ገጽታ፣ የእጆቿ መጉበጥና ከእግሮቿ ረዝሞ መገኘት ጊዜዋን ከዛፍ ዛፍ እየተንጠላጠለች ታሳልፍ ነበር የሚል እሳቤ እንዲያዝ አድርጓል። እንደ ተመራማሪዎቹ አባባል ደፍጣጣ አፍንጫዋ፣ ሰፋ ያለው አገጯ ሉሲን መሰረታቸው አፍሪካ ከሆኑት ቺፓንዚ ከሚሰኙት የዝንጀሮ ዝርያዎች ጋር ያመሳስላታል። ዶክተር ብሉመንሻይ “ሉሲ ከሌሎች ቀደምት የሰው ዘር ግኝቶች በበለጠ አፍሪካ የሰው ዘር መሰረት መሆኗን ያሳያል” ሲሉ ተደምጠዋል።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች፣ በሞሮኮና በደቡብ አፍሪካ የሉሲን ያህል ዕድሜ ያላቸው ባይሆኑም የተለያዩ ቅሪተ-አካላት ተገኝተዋል። ነገር ግን አንዳቸውም የሉሲን ያህል ዕውቅናና ዝና አላገኙም፤ ምክንያቱ ደግሞ ለሰው ልጆች ጥንታዊ አመጣጥ ከእርሷ የተሻለ ፍንጭ የሰጠ አለመኖሩ፣ 40 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ክፍሏ በተሟላ ሁኔታ መገኘቱ ነው። ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዓመታንን ተሻግሮ የሰው ልጆችን አኗኗር፣ ተፈጥሯዊ ሁኔታና አስተሳሰብ ለማሳየትም ከሉሲ የቀደመ አለመኖሩም እንዲሁ።
የሉሲ ወደ አሜሪካ መሄድና ለአምስት ዓመት በዚያው መቆየት ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ተመራማሪዎች በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በአጥንቶቿ የውስጥ ስብራቶች ላይ የ10 ቀናት ጥልቅ የሲቲ ስካን ምርመራ አድርገውላታል፤ ከሶስት ዓመታት በፊትም ስለ አሟሟቷ የደረሱበትን ውጤት ይፋ አድርገዋል፤ ከዛፍ ላይ ወድቃ መሞቷን።
በሉሲ አጥንቶች የውስጥ ስብራቶች ላይ በተደረገው ጥናት ከተገኙት መረጃዎች አንዱ የቀኝ እጇን ከትከሻዋ የሚያገናኘው አጥንት ስብራት ለየት ያለ መሆኑን አሳይቷል። የጥናት ቡድኑን ከመሩት የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጆን ካፔልማን ጋር የሠሩት ኢትዮጵያዊው የፓልዮ አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ዶክተር ሙሉጌታ ፍሥሐ ግኝቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ስብራቱ በአሁኑ ዘመን ሰዎች ከትላልቅ ሕንፃዎች ወይም ከረዥም ገደል ሲወድቁና ለመነሳት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከሚነሳ የአጥንት ስብራት ጋር በጣም እንደሚመሳሰል ነው የገለጹት።
ሌሎቹም የሉሲ የራስ ቅል፣ መንጋጋ፣ የማህፀንና የጎን አጥንቶች፣ የግራ እግር ጉልበትና የቀኝ እግሯ ቁርጭምጭሚት ሉሲ ከትልቅ ዛፍ በመውደቅ ያጋጠሟት የአጥንት ስብራቶች መሆናቸውን፣ በጊዜው የወደቀችበት የሀዳር አካባቢ የዚያን ጊዜ ሥነ-ምኅዳርና የአየር ንብረት ጥናቶች እንደሚያሳዩት አካባቢው ሳራማና አልፎ አልፎ ዛፎች የነበሩበት እንዲሁም በወንዝ ዳር የሚገኙት ደለሎች እርጥበትና ለም አፈር የበዛበት እንደነበር።
ሉሲ በዚያው በደለሉ ቦታ መቀበሯ ደግሞ 40 በመቶ ቅሪተ-አካሏ በጥሩ ሁኔታ እንዲገኝ አድርጎታል። ከአካሏ፣ ከሲቲ ስካን ምርመራ፣ ከመገኛዋ ስፍራ የቀድሞ ሥነ-ምህዳርና የአየር ንብረት መረጃዎች ጥቅል ትርጓሜ መሠረት ሉሲ ለሞት የተዳረገችው ከ12 ሜትር በላይ ከሆነ ረዥም ዛፍ ላይ በመውደቋና ወዲያውም በወንዝ ዳርቻ በሚገኝ ደለል ውስጥ መቀበሯ እንደሆነም ተመራማሪዎቹ ነግረውናል።
እናም የሉሲ ቅሪተ አካል ከተገኘበት ከአስርት ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ስለ ሰው ልጆች አመጣጥ እየተካሄደ ያለውን ምርምር ማገዙን ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ የሰው ዘር መገኛ መሆናቸውን ጭምር።
ይህን እያልን ባለንበት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ይናቆራሉ፤ ባስ ሲልም ግጭቶች ተነስተው ሰዎች ይሞታሉ፤ ንብረትም ይወድማል።
ሃይማኖትም ይሁን ሳይንስ የሰው ዘር መገኛ አንድ መሆኑን እንጂ በየብሔሩ ልዩነት መኖሩን አይነግሩንም። መነሻችን ሳይንሱ ነውና ሳይንሱ እንደሚለው ሉሲ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳትሆን የሰው ልጆችም እናት ናት። የዓለም ህዝቦች በቆዳ ቀለም፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በዕድሜ፣ በሃብት፣ ወዘተ ቢለያዩም ሁሉም ከአንድ ሃረግ ይመዘዛሉ። እናም በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን በብሔር መከፋፈልና "እኔ እለያለሁ" የሚል አስተሳሰብ በመቀየር በኢትዮጵያ ምድር ፍቅርና ሰላም እንዲነግስ ታስቦ ነው ጉዞ ሉሲ የተሰናዳው።
የታሪክ ቁርሾ፣ ቂም-በቀልና ጥላቻን ወደ ጎን በመተው፤ ፍቅርና አንድነትን ደግሞ ከፍ በማድረግ የአስታራቂነት ሚና እንድትጫወት ሉሲ የአምባሳደርነት ሚና ተሰጥቷታል።
ይህን የመሰለ ታላቅ ዓላማ ያነገበችው እመት ድንቅነሽ ታዲያ በነገው ዕለት "ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር" በሚል መርሃ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎችም በሚገኙበት ወደ ትልውድ መንደሯ ይፋዊ አሸኛኘት ይደረግላታል። የድንቅነሽ ድንቅ ጉዞ! መልካም ጉዞ።