የመንግሥታቱ ድርጅት ለሕዝብና ቤት ቆጠራው ውጤታማነት ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥታቱ ድርጅት ለሕዝብና ቤት ቆጠራው ውጤታማነት ድጋፍ ያደርጋል
አዲስ አበባ የካቲት 13/2011 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስነ- ህዝብ ፈንድ ለ4ኛው ዙር አገር አቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቆጠራውን አስመልክቶ ለክልል፣ ለከተማ አስተደደር፣ ለዞንና ለወረዳ የቆጠራ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ያዘጋጀውን ስልጠና ዛሬ መስጠት ጀምሯል።
በየአስር ዓመቱ የሚካሄደውና ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የታቀደው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29 ቀን 2011 እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስነ-ህዝብ ፈንድ /ዩ.ኤን.ኤፍ.ፒ.ኤ/ የኢትዮጵያ ቢሮ ምክትል ተወካይ ሚስ ሳራ ማሳሌ ተቋሙ በህዝብና ቤት ቆጠራ ከዓለም አገራት ጋር በአጋርነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በቅርበት በመስራት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ለ4ኛው ዙር አገር አቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የስነ-ህዝብ ፈንዱ ቁልፍ ሚና ቆጠራው ዓለም አቀፍ መስፈርቶችና ምርጥ ተሞክሮዎችን ባሟላ መልኩ እንዲካሄድ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ ነው ብለዋል።
ተቋሙ የህዝብና ቤት ቆጠራው ሂደትና ውጤት ተአማኒነት እንዲኖረው ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን እንደሚደግፍም አመልክተዋል።
የስነ-ህዝብ ፈንዱ ለኤጀንሲው የቴክኒክ አማካሪ፣ የአየር ካርታና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በመመደብ ቆጠራውን የተመለከቱ ስራዎች እያከናወኑ መሆናቸውንና ተግባሩ ቀጣይነት እንዳለው ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ ለህዝብና ቤት ቆጠራ ስራው የሚያስፈልጉ የተለያዩ መሳሪያዎችና ሶፍትዌር የመግዛትና የመትከል ስራ እያከናወነ መሆኑን ነው ሚስ ሳራ ያስረዱት።
በቀጣይም በኢትዮጵያ የህዝብና የልማት ፖሊሲዎችና መርሃ ግብሮችን የመደገፍ ሂደት እንደሚቀጥል፣ ለዚህም ከመንግስትና ከኤጀንሲው ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የስልጠናው ዓላማ የህዝብና ቤት ቆጠራውን ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ለክልል፣ ለከተማ አስተደደር፣ ለዞንና ለወረዳ የቆጠራ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ማስገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰልጣኞቹ የሚያገኙትን እውቀት በመጠቀም በህዝብና ቤት ቆጠራው ውጤታማ ስራ ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።
እስከ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በሚዘልቀው ስልጠና 1 ሺህ 200 ሠራተኞች እንደሚሳተፉና በቀጣይም ተከታታይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።
አራተኛው ዙር አገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ በየካቲት 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ባሳለፉት ውሳኔ ወደዚህ ዓመት እንዲሸጋገር መወሰኑ ይታወቃል።