የካቲት እና ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
የካቲት እና ኢትዮጵያ
ሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/
በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የካቲት ታሪካዊ ወር ነው፡፡ ታላላቅ አብዮቶችና ታላላቅ ድሎችም በየካቲት ወር ተገኝተዋል፡፡ ዐድዋን ያህል ለጥቁር ህዝቦች ከፍታው ሰማየ ሰማያትን የሚነካ ድል የተገኘው የካቲት ወር በገባ በ23 ቀን ነው፡፡ ይህ በሆነ ከ39 ዓመታት በኋላ በድሉ ሃፍረትን ተከናንቦ የነበረው ፋሽስት ከ30 ሺህ በላይ ዜጎቻችን (የአዲስ አበባ ኗሪዎች ብቻ) በግፍ የተጨፈጨፉትም በየካቲት 12 ነው፡፡ የካቲት ድልም ደምም ነው፡፡
የካቲት የፖለቲካ ግለትና መቀዝቀዝ፣ የአብዮት መነሳት፣ የድል ብስራት ዜና፣ በግፍ መስዋት የመሆን እንዲሁም ዳግም የመነሳት የድል ብርሃን የታየበት ወር ሆኖ እናገኘዋለን። የዓመቱ አጋማሽ-ታሪክ በደማቅ ብዕሩ ይጽፈው ዘንድ የሚያስገድዱ ግዙፍ ሁነቶችን ያስተናገደ ደማቅ ወር ነው የካቲት። የዐድዋ ድል ከተመዘገበ ወዲህ እንኳን የየካቲት 12 ቀን 1929 የፋሺስት ጥቃት፣ የየካቲት አብዮት፣ የካራማራ ድል፣ ... የወሩ መዘከሪያ ሁነቶች ሆነው እናገኛቸዋለን።
የካቲት 12 - የሰማዕታት ቀን
የየካቲት ወር በኢትዮጵያ ላቅ ያለ ታሪካዊ ቦታን የያዘ ነው። የቀደመው የካቲት 12 ቀን 1929ዓ.ም ሲታወስ አካፋና ዶማ፣ ፋስና መጥረቢያ ለሰው ልጅ መጨፍጨፊያነት ውለዋል። አዛውንት እናትና አባቶች ሕጻናትን ጨምሮ በመኖሪያቸው በእሳት ጋይተዋል። ዋይታና ጩኸት፣ የሰቆቃ ድምጾች እሪታና ጣር እያሰሙ ንጹሐን ዜጎች በየመንገዱ፣ በየጉራንጉሩ፣ በየመንደሩ ተዘርግተዋል።
ሰላማዊያኑ ኢትዮጵያዊያን በግፍ ዕልቂት የተፈጁበት ይህ ዕለት ዐርብ ነበር፡፡ ረቡዕ የካቲት 10 ቀን 1929 ዓ.ም ግራዚያኒ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ለሕዝቡም ሞተ ተብሎ የተወራው ስሕተት እንደነበረና ምንም ያለ መሆኑን ለማሳየት፣ ለማረጋገጥ ስለፈለገ በማግሥቱ የካቲት 11 ቀን 1929 ዓ.ም ባስነገረው የጥሪ አዋጅ በማስተላለፍ በአደባባይ ላይ እንዲሰበሰቡ አስደረገ፡፡
ሆኖም የተሰብሳቢው ቁጥር ስላነሰበትና ያሰበውን ያህል ትኩረት እንዳለገኘ ስለተሰማው፣ በማግሥቱ ዐርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ከቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ መልስ ልክ ከጥዋቱ በ4፡00 ሰዓት ሕዝቡ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት እንዲሰበሰብ አዘዘ፡፡ ለነዳያንና ለችግረኞችም ብዙ ሊሬ እንደሚሰጥ ጭምር አስለፈፈ።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ልክ በአራት ሰዓት ይጀመራል የተባለው ፕሮግራም ግብጻዊው አቡን፣ አቡነ ቄርሎስ ታምሜያለሁ ብለው ለአንድ ሰዓት ያህል ዘገዩ፡፡ ወታደር ተልኮ አቡኑ ልክ 4፡55 ሰዓት ቤተ መንግሥት ደረሱ፡፡ ወንበር መጥቶላቸው ከግራዚያኒ በስተቀኝ በኩል ከከፍተኛ የፋሺስት ባለስልጣናት ጎን ተቀመጡ፡፡
ከግራዚያኒም በስተግራ በኩል ጄኔራል ጋሪባልዲ፣ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ፣ ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት እና ከሌሎች ኢትዮጵያን ክደው ለጣሊያን ካደሩ (ባንዶች) ጋር ተቀምጠው ነበር፡፡ ስብሰባው እንደተጀመረ ግራዚያኒ ከፍተኛ ንቀት በተሞላበት ኩራት ተወጣጥሮ ቁና ቁና እየተነፈሰ ኢትዮጵያውያንን ያበሻቅጥ ጀመር። “ይኼው አለሁ!... ሞቷል እያላችሁ የምታወሩትና የምታስወሩት ሁሉ ከንቱ ሟርት ነው፡፡”
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ቦንብ ወደ መድረኩ ቦንብ ወረወሩ፡፡ የመጀመሪያው ቦንብ እንደተወረወረ ብዙዎቹ የመሰላቸው ለስብሰባው ማድመቂያ መድፍ የተተኮሰ ነበር ህዝቡ የመሰለው ፡፡ ሁለተኛው ሲወረወር ግን፣ አቡነ ቄርሎስና ግራዚያኒ መሬት ያዙ፡፡ በስተ ግራ በኩል የነበሩት ሁለት ጥበቃዎች በቦንቡ ተመተው ወዲያውኑ ሞቱ፡፡
ሦስተኛው ቦንብ ሲወረወርም ግራዚያኒ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሊገባ ፊቱን አዙሮ መሸምጠጥ ጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም፤ የሦስተኛው ቦንብ ፍንጣሪዎች በርካታ ቦታ አቆሠሉት፡፡ በፍጥነት ወደ ኦስፒዳሌ ኢታሊያኖ (የጣሊያን ሆስፒታል) የዛሬው “ራስ ደስታ ሆስፒታል” ወሰዱት፡፡
ይህን አስታኮ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. እኩለ ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 14 ቀን 1929 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በግፍ ተፈጁ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚነገረው ቁጥር በአዲስ አበባ ብቻ የተፈፀመውን ግድያ የሚያሳይ ነው፡፡
በፋሺስቱ ግራዚያኒና በግብረ አበሮቹ፣ በከሃዲ ባንዳ ኢትዮጵያውያን ትብብር በመላው ኢትዮጵያ አውራጃችና ቀበሌዎች ባልቴት፣ ሽማግሌ፣ ሕፃን፣ ወጣት፣ ካሕን፣ እስላም፣ ክርስቲያን፣ ማንም ከማንም ሳይለይ ተፈጀ፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩትና በወቅቱ በስፍራው የነበሩት አሃዱ ሳቡሬ በየካቲት 12 ቀን 1947 ዓ.ም እንደገለጹት፤ “ኢትዮጵያን መሬቷን እንጂ ሕዝቧን አንፈልግም” በሚል ዘረኛነት የፈጀውና ያስፈጀው ግራዚያኒ፤ በከተማ ነዋሪ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን ነፍሰ ጡር ሳይቀር እጅግ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ነበር ያስፈጃቸው፡፡
ግድያው በመትረየስና በጠመንጃ ብቻ አልነበረም፡፡ በአካፋ ተጨፍጭፈው፣ በዶማም ተፈልጠው፣ በፋስና በመጥረቢያም ተቆራርጠው የሞቱትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ከቤታቸው ለመውጣትና ለማምለጥ ያልቻሉትን ባልቴቶችና ሽማግሌዎችም ቤቱን የኋሊት እየዘጉባቸው ነበር እሳት ጎጇቸው ላይ የለኮሱባቸው፡፡
በዚህ ለሦስት መዓልትና ለሦስት ሌሊት ሲፈጸም በነበረው ግፍ ወቅት፤ የኢትዮጵያውያኑ ሰማዕታት አስክሬን በገዛ አገሩ ጥርኝ አፈር ተነፍጎ በየጎዳናው ተዘርሮ፣ ደሙም እንደ ሐምሌ ጎርፍ ሲጥለቀለቅ፣ በገዛ ቤታቸው የተቃጠሉትና የቤቱ ቃጠሎ ነበልባል ደግሞ ጢስ እስከ ሰማይ ሲያርግ ማየታቸውን የዐይን ምስክሮች ተናግረዋል፡፡
በአራተኛው ቀን የካቲት 15 ቀን 1929 ዓ.ም. ሁኔታዎች ጋብ ያሉ መሰሉ፡፡ የግራዚያኒም ቁጣ የበረደ መሰለ፡፡ ለከተማዎቹም ጽዳት ሲባል የሰማዕታቱ አስክሬን አፈር እንዲቀምስ ተደረገ፡፡ ብዙዎቹ በቡልዶዘር አማካይነት በጅምላ ተቀበሩ፡፡
እነዚህ የጅምላ መቃብሮች አብዛኛዎቹ ዛሬም በቅጡ አይታወቁም፡፡ የተወሰኑት ግን ለዓጽማቸው ማረፊያና መታሰቢያ ተብሎ በቅድስት ሥላሴ ሃውልት ቆሞላቸዋል፡፡
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከራስ አበበ አረጋይ የአርበኞች ጦር ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ ራስ አበበ አረጋይ ልዩ እንክብካቤ እንዲያገኙ አደረጉ። ቆይተው ግን የነበራቸውን የትምርት ደረጃ በመረዳት ከአገር ውጭ ወጥተው ለአገራቸው ቢሰሩ ይጠቅማሉ ብለው በማሰብ ከስንቅ እና ገንዘብ ጋር ወደ ሱዳን እንዲሄዱ መከሯቸው።
ሆኖም ግን በጉዞአቸው ላይ ሱዳን ሊገቡ ትንሽ ሲቀራቸው ፎቶዋቸው በገጠር ባሉ የፋሺሽት ወታደሮች ሁሉ ተናኝቶ ነበርና በፋሺስቶች ተይዘው በስቅላት ተቀጥተው ሰማዕት ሆኑ።
በኋላ ግን አፄ ኃይለሥላሴ በሱዳን በኩል ጣልያንን ከእንግሊዝ ሰራዊት ጋር ሆነው ድል ሲያደርጉ የአብርሃ እና የሞገስ አስከሬን ተቆፍሮ ወጥቶ አሁን አዲስ አበባ በሚገኘው የቅድስት ስላሴ አርበኞች ሐውልት ስር እንዲያርፍ አድርገዋል።
ከየካቲት 12 ዋይታ 37 ዓመታት በኋላ የዛሬ 45 ዓመት ሌላ ጩኸት! ስለ መብት፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ረሃብ፣ ስለ ድንቁርና አቤት! የተባለበት ጩኸት።
የካቲት 66 አብዮት
አዲስ አበባ በታክሲ አሽከርካሪዎች፣ በመምህራን፣ በሠራተኞች፣ በእስልምና እምነት ተከታዮች፣ በወጣቶች፣ በተማሪዎች፣ በወታደሮች በጥቅሉ በሕዝባዊ አብዮት ተናወጠች። መሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ መብት፣ የሃይማኖት እኩልነት፣ የብሔሮች እኩልነት፣ የሴቶች እኩልነት ከፍ ተደርገው ተጮኸላቸው፣ ተዘመረላቸው።
ልክ የዛሬ 45 ዓመት የካቲት 1966 ዓ.ም. የፈነዳው እሳተ ጎመራ አድማሱን አስፍቶ ኢትዮጵያ ለዘመናት የተዳደረችበትን የዘውድና የአፄ ሥርዓት የገረሰሰበት ሕዝባዊ አብዮት ተወለደ።
የካቲት አዝሎት የነበረው ሕዝባዊ ተስፋ መጠነ ሰፊ ነበር። በረሃብ ዘወትር የሚጠቃው ሕዝባችን በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገበው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ፣ ጤናው እንዲሟላ፣ ትምህርት ያልደረሰው ወገን ትምህርት እንዲያገኝ፣ የነበረው የትምህርት ሥርዓትም የተሟላና ከምርትና ከዕድገት ጋር የተያያዘ እንዲሆን፣ ንጹህ ውሃ፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ተስፋና ምኞትን የካቲት ተሸክሞ ነበር።
ሁሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ደግሞ የካቲት ፖለቲካዊ ተስፋም አንግቦ ነበር። ማን እቅዱን ያወጣል? ማን እቅዱን ይተቻል? ማን እቅዱን ያስፈጽማል? ማንስ ተፈጻሚነቱን ይከታተላል? ለሚሉትና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ሁሉ የካቲት ተስፋዊ መልስ ሰጥቶ ነበር።
ሥልጣን የሕዝብ እንዲሆን፣ አገሪቱ በሕዝብ በተመረጡ ዜጎች እንድትተዳደርና ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት፣ ዳኝነት ፍትሃዊ በሆነና ነፃ በሆነ መልኩ እንዲስፋፋ፣ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች፤ ማለትም በፖለቲካ ድርጅትም ሆነ በሠራተኛ ማኅበር የመደራጀት መብት እንዲከበር፣ በነፃነት የመጻፍ፣ የመወያየት ... ወዘተ መብቶች ያለገደብ እንዲከበሩ የካቲት ተስፋውን ሰንቆ ነበር።
እነሆ ወርሃ የካቲት 1966 ዓ.ም. 45 ዓመት። በወርሃ የካቲት 66 የተወለደ ሕፃን 45 ዓመት ሞልቶታል። ከወጣትነት አልፈው አባባ፣ እማማ የተባለ እናትና አባቶችን የካቲት አድርሷል።
የካቲት 66 ኢትዮጵያን የልጆቿ ለማድረግ የትግል ችቦ የተለኮሰበት፤ አርሶ አደሮች ከባላባታዊ የጭሰኝነት ሕይወት ለመላቀቅ ያመጹበት፣ ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ የተጠየቀበት፣ መምህራን አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ «ሴክተር ሪቪው»ን የተቃወሙበትና በማህበራቸው ደህንነት የሞገቱበት፣ ታክሲ ነጂዎች በነዳጅ ጭማሪ ምክንያት ሥራ ያቆሙበት፣ ሙስሊሞች የሃይማኖት እኩልነት ብለው በአደባባይ ሰልፍ የወጡበት፣ ተማሪዎችና ተራማጅ ኃይሎች “መሬት ለአራሹ” መፈክርን ከፍ አድርገው ሥር ነቀል ለውጥ የጠየቁበት።
ይህን ከዳር እስከ ዳር የተንቀሳቀሰ ሕዝባዊ ማዕበል መለዮ ለባሹ ያጀበበት።
ወታደራዊ መንግስት ከአንዳንድ መካሪዎቹ ጋር በመሆን በዙፋኑ ዙሪያ የተሰለፈው የሻለቃ በታች የጦር ኃይሎች ወኪል መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. በጊዜያዊነትና በሞግዚት አስተዳደር ስም የመንግሥት ሥልጣኑን ጨበጠ።
የየካቲቱ 66 ሕዝባዊ አብዮት ወደ ወታደራዊ አብዮት ተሸጋገረ። በሦስት ወር ጉዞውም የንጉሱን 60 ሹማምንት ያለፍርድ ገድሎ የፍየል ወጠጤ ጨፈረ። ንጉሱን ከስልጣን በማውረድ እራሱን ደርግ ብሎ በመሰየም ብቸኛው የኢትዮጵያ መንግስት ፈላጭ ቆራጭ ሆነ።
አማካሪዎቹም በዚሁ ሹም ሽር ከስልጣን ተካፋይነት ወደ ሁለተኛ ደረጃ አማካሪት ወረዱ። ደርግም ለሚቀጥለው 17 ዓመት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር መጀመሪያ “ኢትዮጵያ ትቅደም” በኋላ “ሶሻሊስት ሪፑብሊክ” ፈጠርኩ ቢልም ገና ከጅምሩ ተቃዋሚውን ጸጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት ያወጣው የዴሞክራሲ መብት እገዳ አዋጅ እያደር ቀውስ ውስጥ ከተተው።
ወታደራዊ ባህሪውና ጦረኝነቱ በማርሽና በቀረርቶ ታጀበ። በዋና ተቃዋሚነት ኢሕአፓ በደርጉ ስርም እነ መኢሶን፣ ወዝ ሊግና ሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ የአብዮት ተውኔት መድረክ ላይ ያዋጣል ያሉትን የትግል ስልትና ዘዴ ቢከተሉም “ሽንኩርት የባህሪውን ይሸታል” እንዲሉ የደርግ መንግስት ወታደራዊ ባህሪው አይሎበት ባልተወለደ አንጀቱ የመጀመሪያዎቹን ከርቸሌ፤ የቀጠሉትን በየጎዳናው ዳርቻ፤ ከዚህ የተረፉትን በደርግ ጽህፈት ቤት በማነቅ፡ ገሎ ወደ ታሪካዊ ፍርድ ሸንጎ ማለፉን 'ያ ትውልድ' በሚል የተዘጋጀው የክፍሉ ታደሰ ተከታታይ ቅጽ ያስነብበናል።
የደርግም መንግስት በስልጣን ዘመኑ የተነሱትን አበይት ጥያቄዎች ለመመለስ ከሰላም ውይይት ይልቅ ጦር ሰባቂ ጎራዴ ታጣቂ በመሆኑ ኤርትራን አስገንጥሎ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ንብረት አሳጥቶ፣ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ለረሀብ አጋልጦ፣ ከ400 ሺህ እስከ 600 ሺህ ህዝብ ገድሎ ካገር ሸሽቶ፣ ፈርጥጦ ሄዷል።
ያሁሉ አልፎ ዛሬ ላይ ደርሰናል። የአሁኑ ትውልድም ከወርሃ የካቲት 1966 ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ትምህርት በመቅሰም ከሕዝብ ብሶትና ስቃይ ገንፍሎ የሚነሳ ግብታዊ እንቅስቃሴ እንዳይቀለበስ ተደራጅቶና ተዘጋጅቶ የተቀናጀ ትግል ማድረግ እንደሚገባ ግንዛቤ ሊወስድ ይገባዋል እንላለን።
የካቲት ያስተማረን ያለትግል መብት እንደማይገኝ ነው። ባለፉት ብዙ የካቲቶች አልመን ያጣናቸውን የተስፋ ጮራዎች መልሰን ለማድመቅ የጎደሉትንና በመሙላት ተስፋውን ወደ ድል ለመለወጥ መትጋት የወጣቱ ትውልድ ፈንታ ነው።
ለመጠቅለያችን “ወርኃ የካቲት በረከትና መርገምት” በማለት አባ ገንባው ዘቦሌ በሪፖርተር ጋዜጣ ያሰፈሩትን ጽሑፍ እንመልከት።
የካቲት 20 ቀን 1966 ዓ.ም.፣ ከ45 ዓመት በፊት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ከነካቢኔያቸው ‹‹…የመለዮ ለባሹንም ሆነ ሌላውን ሕዝባዊ ጥያቄ ለመፍታት ካቅማችን በላይ ሆኗልና ግርማዊነትዎ አስፈላጊውን ውሳኔ ያድርጉ›› በማለት የካቢኔ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል፡፡
ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ይህ ቀን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአምስት ዓመት በላይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በኋላ፣ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ያቀረቡበት ዕለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ በተለያዩ ዓመታት የየካቲት ወሮች፣ በአገር ደረጃ የተከሰቱ ጉልህ መርገምትና በረከት ነበሩ፡፡
የትግራይ ወጣቶች፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ትግል ወደ ደደቢት ያመሩት ከ43 ዓመት በፊት በወርኃ የካቲት 1967 ዓ.ም. ነበር፡፡
አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ ቦምብ በመጣል ያደረጉትን ሙከራ ተከትሎ፣ የፋሺስት ጣሊያን ወታደሮች 30 ሺሕ ንፁኃን ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፉት ከ82 ዓመት በፊት፣ በወርኃ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነበር፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት የተቀጣጠለው በዚሁ የካቲት ወር፣ የጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ካቢኔም ሥልጣን የለቀቀው ከ44 ዓመት በፊት በወርኃ የካቲት 20 ቀን 1966 ዓ.ም. ነበር፡፡
ከ100 ሺህ ያላነሱ ወታደሮች በተሠዉበት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሻዕቢያ እጅግ እጅግ ይመካበት የነበረውን የባድመን ምሽግ ደምስሶ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል የተቀዳጀውን በወርኃ የካቲት 1991 ዓ.ም. ነበር፡፡
የኢጣሊያን ቅኝ አገዛዝ መንግሥት ሰራዊት ኢትዮጵያን ወርሮ ለመያዝ በዓድዋ ግንባር የሰነዘረውን ጥቃት፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት አንድ ጀንበር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተዋግቶ በመደምሰስ፣ አንፀባራቂ ድል የተቀዳጀው በወርኃ የካቲት 1888 ዓ.ም. ነበር፡፡
ክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥራና ኃላፊነት ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ያስታወቁት፣ በዚሁ ወርኃ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡
ከእነዚህ ስድስት የታሪክ ክስተቶች የትኛው በረከት፣ የትኛው መርገምት እንደ ሆነ ለይቶ የመወሰኑ የቤት ሥራ የአንባብያን ድርሻ ይሆን ዘንድ በመፍቀድ (በመተው) ተሰናበትሁ፡፡