ቀጥታ፡

የውጭ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው ጋር በሽርክና ቢሰሩ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስ ያግዛል ተባለ

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 በኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ አቻዎቻቸው ጋር በሽርክና መስራታቸው አገሪቱ ለግንባታ ግብዓት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማዳን የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተባለ። 

'ላይኮን'  የተሰኘ የግንባታ ግብኣት አምራች ድርጅት 'ኤም ሲ ባው ክሜ ' ከተሰኘ የጀርመን ኩባንያ ጋር በሽርክና ለመስራት ዛሬ ውል ተፈራርሟል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንሲቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር አርጋው አሻ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአገሪቱ በአብዛኛው የግንባታ ግብዓት ከውጭ የሚገባ ነው።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2016/17 ብቻ የግንባታ ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት ወደ 180 ቢሊዮን ብር ያህል ወጪ በውጭ ምንዛሪ ማድረጓን  አንስተዋል።

በዘርፉ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና መስራት ይህንን ወጪ ከመቀነስ አንጻር ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ዶክተር ኢንጂኒየር አርጋው  ተናግረዋል።

በግንባታው ዘርፍ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው ኩባንያዎች ጋር መስራት የውጭ ምንዛሪን ከማዳን ባሻገር የዘርፉ ተግዳሮት የሆኑትን የግንባታ መዘግየት፣ የጥራት መጓደል፣ የኃብት ብክነትና የግንባታ ወጪዎች ከተያዘው ዕቅድ በላይ መሆንን የመሰሉ ችግሮችን ከመፍታት አንጻርም ያለውን ሚና ገልጸዋል።

የ'ላይኮን' ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደምሴ ኃይለማርያም እንደገለጹት የጀርመኑ ኩባንያ የድርጅቱን 70 በመቶ ድርሻ በመያዝ በሽርክና ለመስራት ነው ስምምነት ያደረገው። 

በማምረቻው ዘርፍ የተሰማራው ድርጅቱ  በግንባታው እውቅና ካለው የአውሮፓ ኩባንያ ጋር በጋራ መስራቱ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ጨምሮ የማምረት አቅሙን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

በግንባታው ዘርፍ ያለውን የሰው ሀይል እጥረት፣ የግንባታ ግብዓት አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን ከመፍታት አኳያም ኩባንያው በኢትዮጵያ መሰማራቱ ይጠቅማል ሲሉ ጠቅሰዋል።

የ'ኤም ሲ ባው ክሜ' ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ኒኮላስ ሙለር በበኩላቸው 58 ዓመታት አድሜ ያለው ኩባንያቸው ከ40 በላይ አገራት ውስጥ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ አቅምን ለማጠናከር በስፋት የመስራት ዕቅድ እንዳለውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም