ቀጥታ፡

በእስቴ ወረዳ መስጊድ በማቃጠል የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች ጉዳይ በሕግ እየታየ ነው

ባህርዳር  የካቲት 12/2011 በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ መስጊድ በማቃጠል የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች ጉዳይ በሕግ እየታየ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

መስጊዱን መልሶ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።

ድርጊቱን በበላይነት ሲመሩትና ሲያስተባብሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን የመምሪያው የወንጀል ምርመራ ዋና የሥራ ሂደት መሪ ምክትል ኮማንደር ክንዱ ወንዴ ዛሬ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

ፖሊስ ወንጀሉ ከተፈፀመ ጊዜ አንስቶ ጉዳዩን የማጣራት ሥራ ሲያከናውን መቆየቱንም አስረድተዋል።

በድርጊቱ እጃቸው ያለባቸውን ተጨማሪ ሰዎች ለመቆጣጠር በአማራ ክልል እስከ ወረዳ በተቋቋመ ቡድን ሥራው ቀጥሏል ብለዋል።

በወረዳው የተቃጠሉትን መስጊዶችን መልሶ ለመገንባት የክርስትናና የእስልምና እምነቶች ተከታዮች በጋራ በመሥራት ላይ  እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

በወረዳው ወደ ሰላም መመለሱን ምክትል ኮማንደር ክንዱ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣የኢትዮጵያ ካቶላካዊት ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና እምነት አባቶች  ድርጊቱን ማውገዛቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም