ከተሞች የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን የራሳቸውን ገቢ ማሳደግ እንዳለባቸው ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን የራሳቸውን ገቢ ማሳደግ እንዳለባቸው ተጠቆመ
ጅግጅጋ የካቲት 12/2011 የኢትዮጵያ ከተሞች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ለማካናወን የራሳቸውን ገቢ ማሳደግ እንዳለባቸው ተጠቆመ።
በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ያለው ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በኤግዚብሽን እና በፓናል ውይይት ቀጥሏል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የከተሞች ፋይናንስ ማሻሻያ ፈንድ ሞቢላይዜሽን ኃላፊ አቶ አምላኩ አዳሙ በፓናሉ ላይ የከተሞች መሰረተ ልማትና የተቋም ልማት ፕሮግራምን አስመልክተው ለውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በእዚህ ወቅት እንዳሉት በከተሞች እየተፈጠረ ያለው የመሰረተ ልማት ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ ነው።
ይህንን የከተሞች ፍላጎት በመንግስትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት በሚገኙው ድጋፍና እርዳታ ብቻ መመለስ እንደማይቻል አመልክተዋል።
"ከተሞች የሚሰጡትን የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት በማሳድግ ገቢ የማሰባሰብ አቅማቸው ማጠናከር ይኖርባቸዋል" ብለዋል።
አቶ አምላኩ እንዳሉት ለከተሞች መሰረተ ልማትና የተቋም ልማት ፕሮግራም ከመንግስትና ከዓለም ባንክ በተገኘ 416 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ሆነዋል።
"ፕሮግራሙ ለስድስት ዓመታት በተካሄደባቸው 18 የተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች 670 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ 588 የውሃ መውረጃ ካናሎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል" ብለዋል።
የፓናል ውይይቱን የመሩት የደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም በበኩላቸው ከተሞች ከመሬት ሊዝና ከውስን አገልግሎት መስክ የሚያገኙትን ገቢ በቀጣይ ማሳዳግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ከተሞች የሚታይባቸውን የመሰረተ ልማት እጥረቶች በመፍታት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ለነዋሪዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆኑ የራሳቸውን የገቢ ምንጭ ሊያጎለብቱ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ አቶ መሀመድ አህመድ ህብረተሰቡም ሆነ የከተሞች አመራር ስለከተማ የውስጥ ገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በፕሮግራሙ በጅግጅጋ ከተማ ለወጣቶች ለመስጠት የታቀደው የሥራ ዕድል ለባለሀብቶች በመሰጠቱ ሥራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
በጅግጅጋ ከተማ በፕሮጅክቱ የተሰሩ የውስጥ ለውስጥ የጌጠኛ ድንጋይ መንገዶች ከፍተኛ የጥራት ችግር እንደሚታይባቸውም አቶ አህመድ አስታውቀዋል።