ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 8ኛ ዓመት መታሰቢያ ጊዮርጊስና ቡና ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ  የካቲት 12/2011 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን ስምንተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለ6ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ የሸገር ደርቢ ተፋላሚ ክለቦች እንደሚሳተፉ ምክር ቤቱ አስታወቀ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጋራ የተዘጋጀው የእግር ኳስ ውድድር ከየካቲት 22 እስከ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በውድድሩ የሸገር ደርቢ ተፎካካሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ከክልል አዳማ ከተማና ሲዳማ ቡና ይሳተፋሉ።

በመክፍቻው ጨዋታ ሐሙስ የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ከቀኑ 11 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ይገናኛሉ።

የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ለዋንጫ የሚጫወቱ ሲሆን በዚሁ ቀን ከዋንጫ ጨዋታው በፊት ለደረጃ ያለፉ ክለቦች ይጫወታሉ።

የውድድሩ ዓላማ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና ከጨዋታው የገንዘብ ገቢ ለማሰባሰብ እንደሆነም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ባለፉት  ዓመታት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር  ተሰብስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም