ቀጥታ፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጤና ጣቢያዎች ያቋቋማቸው ዘመናዊ የማዋለጃ ማዕከላት ሥራ ጀመሩ

ጎንደር  የካቲት 12/2011 ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት ያጋጠመውን ጫና ለማቃለል በጎንደር ከተማ ጤና ጣቢዎች  ያቋቋማቸውን ዘመናዊ የማዋለጃ ማዕከላት ስራ አስጀመረ፡፡

ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በከተማው ሁለት ጤና ጣቢያዎች የተቋቋሙት የማዋለጃ ማዕከላት በቀን እስከ 20 የሚደርሱ እናቶችን የማዋለድ አቅም ሲኖራቸው 100 ለሚደርሱ እናቶችም የእርግዝና ክትትል ምርመራ ለማድረግ ያስችላሉ ተብሏል፡፡

ማዕከላቱ ዛሬ በይፋ ሲከፈቱ የተገኙት የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሲሳይ ይፍሩ እንዳሉት የማዕከላቱ ሥራ መጀመር ሆስፒታሉ በየእለቱ እስከ 70 የሚደርሱ ነፍሰ ጡር እናቶችን በማዋለድ ይደርስበት የነበረውን ጫና ለማቃለል ያስችላል፡፡

ዶክተር ሲሳይ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ 400 ለሚደርሱ ነፍሰጡር እናቶች በየእለቱ የእርግዝና ክትትል የሚያደርግ ሲሆን በማዋላጃ ክፍሎች ጥበት ነፍሰ ጡር እናቶች ምጥ እስኪጀምራቸው ድረስ ኮሪደር ላይ ጭምር ወረፋ እንዲጠብቁ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ የገጠመውን ጫና ለማቃለል በጎንደር ጤና አጠባበቅ ጣቢያና በሎዛ ማርያም ጤና ጣቢያ በማህጸንና ጽንስ ሽፔሻሊስቶች፤ በቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችና አዋላጅ ነርሶች የተደራጁ የማዋለጃ ማዕከላት ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡

የማዋለጃ ማዕከላቱ የነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያ፣ የጽንስ ምርመራና ነፍሰ ጡር እናቶችን በቀዶ ሕክምና ማዋለድ የሚያስችሉ ጽዱ የማዋላጃ ክፍሎች የተሟሉላቸው ናቸው፡፡

ወላዶችንም በየእለቱ የሚያመላልሱ አንቡላንሶችም ለማዋለጃ ማዕከላቱ በቋሚነት መመደቡን ነው የገለጹት፡፡

"ማዕከላቱ በየቀኑ 20 የሚደርሱ ነፍሰ ጡር እናቶችን በቀዶ ህክምና ጭምር የሚያዋልዱ ሲሆኑ 100 ለሚሆኑ ነፍሰጡር እናቶችም በየእለቱ የእርግዝና ክትትልና ምርመራ አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል፡፡

ከጎንደር ከተማ ውጪም የመተማና የደባርቅ ሆስፒታሎችን በሰው ኃይል፣ በመድኃኒትና በህክምና መሳሪያዎች ጭምር በመደገፍ የሆስፒታሉን ጫና ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ሆስፒታሉ ከአማራ ክልል ውጪ ከቤንሻንጉል ክልል ጨምሮ ለሚመጡ እስከ 7 ሚሊዮን ለሚደርሱ ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

የሆስፒታሉን አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ከዩንቨርሲቲው በጀትና ከውጪ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የማዋለጃ ማእከላቱ ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው "የማዋለጃ ማእከላቱ ቀልጣፋና ከእንግልት ነጻ የሆነ የወሊድ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል፡፡" ብለዋል።

በጎንደር ጤና ጣቢያ የእርግዝና ምርመራ ለማድረግ የመጡት ወይዘሮ ማሬ አባይ ከዚህ ቀደም የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት በሆስፒታል ወረፋ በመጠበቅ መጉላላት ይደርስባቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በአቅራቢያቸው የተከፈተው የማዋለጃ ማዕከል የነፍሰጡር እናቶችን እንግልት የሚያስቀርና የጨቅላ ህጻናትን ደህንነት የሚያስጠብቅ በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

"የማዕከላቱ መከፈት ነፍሰ ጡር እናቶች በአቅራቢቸው የወሊድ አገልግሎት አግኝተው ህይወታቸውን ለመታደግ ያስችላል" ያሉት ደግሞ ሌላዋ ነፍሰ ጡር ወይዘሮ ሞሚና ሰይድ ናቸው፡፡

በማዋለጃ ማእከላቱ ስራ የማስጀመር ስነ-ስርአት ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም