ቀጥታ፡

አምቦ የኢትዮጵያን ባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 አምቦ 16ኛውን የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድርና 12ኛውን የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ታስተናግዳለች።

"የባህል ስፖርት ተሳትፏችን ለሠላምና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ ከየካቲት 16-24 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ከስድስት ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚውጣጡ 550 ተሳታፊዎች ይገኛሉ።

በ13 ዓይነት የባህል ስፖርቶች ውድድር የሚካሄድ ሲሆን ገበጣ፣ ገና፣ ፈረስ ጉግስ፣ ቀስት፣ ኩርቦ፣ ቡብና ሻህ ስፖርቶች ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሰለሞን አስፋው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የስፖርት ውድድሩና ፌስቲቫሉ ዓላማ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቱባ ባህሎቻቸውን ማስተዋወቅና ልምድ መለዋወጥ ነው።

የኢትዮጵያን ባህላዊ ስፖርቶች በአዲስ ስርዓትና ደንብ ታሪካዊነታቸውን ሳይለቁ ለማዘጋጀት፣ ለማስፋፋትና ተወዳጅ ለማድረግ ውድድሩና ፌስቲቫሉ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ከውደድሩ መሪ ቃል ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ባህል ጨዋነት የተሞላበትና ጠንካራ የትብብር መንፈስ ያለው በመሆኑ የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫሉ የአገሪቱ ሰላምና የህዝቡም አንድነት የሚታይበት እንደሚሆን ተናግረዋል።

''ኢትዮጵያ ያላትን አኩሪ ባህል በማስተዋወቅ በውድድሩና ፌስቲቫሉ ትንሿ ኢትዮጵያ እንደምትታይ እምነቴ ነው'' ብለዋል።

ቀደም ሲል በተካሄዱ ውድድሮችና ፌስቲቫሎች በ11 የባህል ስፖርቶች ውድድር መካሄዱን አስታውሰው በዘንድሮው ውድድር ድብልቅ ኩርቦና ድብልቅ ቀስት ወንዶችና ሴቶች አንድ ላይ ሆነው የሚወዳደሩባቸው መስኮች መካተታቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሌ በበኩላቸው ውድድርና ፌስቲቫሉን የተመለከቱ በርካታ ሥራዎችን እንደተከናወኑ ገልጸዋል።

ለተሳታፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ፌስቲቫሉና ውድድሩ በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲካሄድ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

ለዳኞች ተከታታይ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ውድድሮች በባህል ስፖርት ኢንስትራክተሮችና በሁለተኛ ደረጃ ዳኞች እንደሚመሩም አክለዋል።

የአብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል የአዘጋጇ አምቦ ቅድመ ዝግጅትም ተገምግሟል።

ከተማዋ ውድድሩንና ፌስቲቫሉን ማዘጋጀት የሚያስችሏትን ተግባራት ማጠናቀቋንም ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፀጥታ ችግር ምክንያት የውስጥ ውድድር ባለማድረጉ በውድድሩና በፌስቲቫሉ እንዳማይሳተፍ ለፌዴሬሽኑ ማሳወቁንም ገልጸዋል።

የጋምቤላና የሱማሌ ክልሎች በውድድሩ እንደሚሳተፉ አሳውቀው የነበረ ቢሆንም ምክንያታቸውን ሳይገልጹ እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸውን የገለጹት አቶ በላይነህ ክልሎች ላለፉት ሦስት ዓመታት በተካሄዱት ፌስቲቫሎችና ውድድሮች አለመሳተፋቸውን አመልክተዋል።

ፌስቲቫልና ውድድሩን የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል።

አምቦ በ2001 ዓ.ም ሰባተኛውን የባህል ስፖርት ውድድሮችና ሦስተኛውን የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ማስተናገዷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድርና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በ2010 ዓ.ም በአገሪቱ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ሳይካሄድ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም