ኢትዮጵያና አንጎላ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ

93

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 ኢትዮጵያና አንጎላ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ አዲስ የተሾሙትን የአንጎላን አምባሳደር ፍራንሲስኮ ጆስ ዳክሩዝን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል።

በነበራቸው ውይይትም ኢትዮጵያና አንጎላ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ሚኒስትር ዴዔታዋ ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ሁለቱ አገሮች የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን በማቋቋም በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በግብርና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መስኮች በትብብር ለመስራት መስማማታቸውንም አውስተዋል።

የሁለቱ አገሮች የጋራ የባለሙያዎች ስብሰባ በቅርቡ ለማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረሱንም ወይዘሮ ሂሩት ገልጸዋል። 

አምባሳደር ፍራንሲስኮ ጆስ በበኩላቸው አንጎላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራ ወዳጅነት ለማስቀጠል ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለግንኙነቱ ጠንካራ መሰረት የጣለ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ በቀጣይ ሁለቱ አገሮች የጋራ የትብብር ስምምነት በመፈራረም  በግብርና፣ በቱሪዝም እና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መስኮች በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

አትዮጵያና አንጎላ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን አንጐላ በ1971 ዓ.ም. ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች።

በዚምባቡዌ ሐራሬ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአንጎላም ተጨማሪ የድፕሎማሲ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም