ለ4ኛው የህዝብና ቤት ቆጠራው ስኬት መላው ዜጋ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

77

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011በኢትዮጵያ ከወር በኋላ የሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ የተሳካ እንዲሆን መላው ዜጋ የሚጠበቅበትን ትብብር እንዲያደርግ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ።

በየአስር ዓመቱ የሚካሄደውና ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የታቀደው የህዝብና ቤት ቆጠራ በመጪው መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በመላው አገሪቷ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። 

ለዚህም 152 ሺህ የቆጠራ ቦታዎች፣ 182 ሺህ ቆጣሪዎችና 38 ሺህ ተቆጣጣሪዎች እንደዚሁም ለቆጠራው የሚያመቹ የቆጠራ ቦታ ካርታዎች ተዘጋጅተዋል።

በኤጀንሲው የኦሮሚያ የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ፀሀፊ አቶ ሼኮ ጉሩ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገለግሎት እንደገለፁት ቆጠራው በአገሪቱ ትክክለኛ የልማት እቅዶችንና ፖሊሲዎችን በመቅረፅ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መረጃ ለመሰብሰብ ወሳኝ ነው።

በመሆኑም ህዝቡ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ለስኬቱ የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት ነው የኮሚሽኑ ፀሃፊ ያሳሰቡት።  

ቆጠራው በትክክልና በጥራት መካሄድ የአገሪቷን ሁለንተናዊ ተጨባጭ ሁኔታ በማመላከት ከአገር ባሻገር ዓለም አቀፍ ፋይዳም ያለው በመሆኑ  መረጃው በትክከል መሰባሰብ እንዳለበት ፀሀፊው ገልጸዋል።  

የቆጠራውን ጥራት ለማረጋገጥ ታስቦ በተካሄደው የሙከራ ቆጠራ በከተሞች አካባቢ ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦች 'ተካራዮች ቤት ይወስዱብናል'  በሚል የተሳሳተ እሳቤ በመነሳት ተከራዮቹን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ የማይሆኑበት ሁኔታ ማጋጠሙን ጠቅሰዋል።

እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን የገለፁት አቶ ሼኮ ጉሩ፤ ባለቤቶች በቤታቸው ተከራይተው የሚኖሩትን ዜጎች የማስቆጠር ግዴታ እንዳለባቸው፤ ይህም በቤት ባለቤትነታቸው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማስተካከል መሆኑን አንስተዋል።

በጎዳና ላይ የሚኖሩና ተፈናቅለው ወደየቄያቸው ያልተመለሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በያሉበት ለመቁጠር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄደው በዲጂታል ሳተላይት ስርዓት በመታገዝ ነው ያሉት አቶ ሼኮ፤ የአፋር ስምጥ ሸለቆን ጨምሮ ለዲጂታል ስርዓቱ አመቺ ባልሆኑ አንዳንድ የአገሪቷ ክፍሎች ቆጠራው የሚካሄደው ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር መሆኑን ገልጸዋል። 

ቆጠራውን የሚያካሄዱት ከየወረዳው የተውጣጡ የጤናና ግብርና ባለሙያዎች እንደዚሁም መምህራን  ናቸው።

ቆጠራውን ቀልጣፋ፣ ጥራቱን የጠበቀና የተዋጣለት ለማድረግ በማዕከልና በክልሎች  የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ተቋቁሟል።

ስለቆጠራው ለህዝቡ ተከታታይ መረጃና ግንዛቤ  የሚሰጥ የኮሚዩኒኬሽን ኮሚቴ መዋቀሩንም አክለዋል።

ለመቆጠርና መረጃ ለመስጠት አንዲሁም ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆን በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑንም አንስተዋል። 

ከቆጠራው ጋር በተያያዘ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችና ውዥምብሮች ቆጠራውን ሊያስተጓጉል ይችላል፤ በመሆኑም ከዚህ ዓይነቱ ተግባር መቆጠብ እንደሚገባም አሳሰበዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የህዝብና ቤት ቆጠራ የተካሄደው በ1976 ዓ.ም ሲሆን በ1987 እና በ1999 ዓ.ም ሁለተኛውና ሶስተኛው ቆጠራዎች  ተካሂደዋል። 

በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት በየአስር ዓመቱ የህዝብና ቤት ቆጠራ እንዲካሄድ ተደንገጓል። 

በዚህም መሰረት አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ የነበረበት ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆንም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋለው የሰላም ችግር እስካሁን እንዲቆይ አስገደዷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም