በኩታበር ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ በ11 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
በኩታበር ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ በ11 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደረሰ
ደሴ የካቲት 12/2011 በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ ዛሬ በደረሰ የትራፊክ አደጋ በ11 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንደገለጸው አደጋው የደረሰው ከኩታበር ከተማ ወደ 06 የገጠር ቀበሌ 10 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው የጭነት ተሽከርካሪ 15 ሜትር ጥልቀት ካለው ገደል ውስጥ በመግባቱ ነው።
ከጠዋቱ አምስት ሰአት ገደማ በደረሰው አደጋ በተሽከርካሪው ላይ የነበሩት ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪው ከባድ የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠማቸው የጽህፈት ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ቡድን መሪ ኢንስፔክተር ከድር መሐመድ አስረድተዋል።
የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-51167 ኢት በሆነው ተሽከርካሪ ላይ አደጋው የተከሰተው በፍጥነት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።የአደጋውን ዋነኛ መንስዔ ለማጣራት ግን ምርመራው ይቀጥላል ብለዋል።
በዞኑ ጃማ ወረዳ ከሁለት ሳምንታት በፊት በደረሰ የተሸከርካሪ አደጋ የሰባት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፤ በ24 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት አደጋ መድረሱ ይታወሳል።