ኢትዮጵያዊያኑ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርተኞች በግብፅ የግል የበላይነት ውድድር ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያኑ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርተኞች በግብፅ የግል የበላይነት ውድድር ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 ኢትዮጵያዊያኑ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርተኞች ከነገ በስትያ በግብፅ ሁርጋዳ ከተማ በሚካሄደው የG2 የግል የበላይነት ውድድር ይሳተፋሉ።
የግብፅ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ለ6ኛ ጊዜ የሚያካሄደው ውድድር በአዋቂዎች 327 በታዳጊዎች 261 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል።
ሰለሞን በጋሻው በ68 ኪሎ ግራም፣ ታሪኩ ግርማ በ63 ኪሎ ግራም፣ ሰለሞን ቱፋ በ54 ኪሎ ግራም የክብደት ዘርፎች እንደሚወዳደሩ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ለኢዜአ ገልጸዋል።
በማስተር አዲሱ ኡርጌሳ አሰልጣኝነት ልምምድ እያደረጉ መሆኑንና ከነገ በስቲያም ወደ ውድድሩ ስፍራ እንደሚያቀኑ ጠቁመዋል።
በግብጽ ሁርጋዳ ከተማ የሚካሄደው የG2 የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ውድድር ከየካቲት 14-17 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል።
ውድድሩ የሚካሄደው በአዋቂ ወንዶች ከ54-87 ኪሎ ግራም፣ በአዋቂ ሴቶች ከ46-73 ኪሎ ግራም፣ በታዳጊ ወንዶች ከ33-65 ኪሎ ግራም፣ በታዳጊ ሴቶች ከ29-59 ኪሎ ግራም የክብደት ዘርፎች ነው።
በሌላ በኩል በቱርክ አንታሊያ ከተማ ከየካቲት 4-9 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የቱርክ የG1 የወርልድ ቴኮንዶ የግል የበላይነት ውድድር ሰለሞን ቱፋ አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱን አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል።
ሰለሞን ቱፋ በውድድሩ የፍጻሜ ጨዋታ የኡዝቤኪስታኑን ባካሮም አብዱላኤቭን አሸንፏል፤ በውድድሩ የቱርክ፣ አዘርባጃንና ኡዝቤኪስታን ተጋጣሚዎቹን በማስተር አዲሱ ኡርጌሳ ታግዞ በአስገራሚ ብቃት ማሸነፉንም ጠቅሰዋል።
ሰለሞን በዚያው በአንታሊያ በተካሄደው 4ኛው የአውሮፖ የፕሬዚዳንት ዋንጫ ውድድርም እስከ ሩብ ፍጻሜ መጓዝ ችሏል።
ሰለሞን ቱፋ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ በመሆን ኢትዮጵያን እያስጠራ ያለ ስፖርተኛ ሲሆን ባለፈው ዓመት በሞሮኮ አጋዲር ከተማ በተካሄደው የአፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮናና የፕሬዚዳንት ዋንጫ አሸንፏል።
የኮሪያዊያን የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ጥበባዊ ስልቶችን ያካተተ ክንዋኔ ነው።
አዕምሮና ሰውነት ማሰልጠንን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ውጤት በማስገኘት አገሪቷን በማስጠራት ላይ ይገኛል።