ቀጥታ፡

የሰማዕታት ቀን ሲታወስ

አዲስ አበባ  የካቲት 12/2011 የዛሬ 82 ዓመት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አሰዛኝ ታሪክ ተፈጸመ። በ1929 ዓ.ም የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ዳግም በተቆጣጠረበት ወቅት።

በወቅቱ የጦሩ መሪ ግራዚያኒ በቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስጦታ እሰጣለሁ በሚል በተሰበሰበበት ወቅት በሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ የእጅ ቦንቦች ተወረወሩ።    

በጥቃቱ ግራዚያኒን ጨምሮ የጣልያን ጦር አመራሮች ጉዳት ደረሰባቸው ይህን ተከትሎም በግራዚያኒ የሚመራው የጣሊያን ጦር በወሰደው የአጸፋ ርምጃ ጾታና ዕድሜ ሳይለይ ኢትዮጵያዊያንን ገደለ አቆሰለ።   

የታሪክ ድርሳናት እንደሚሳዩትም በዕለቱ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን መስዋዕት ሆነዋል።

የጣሊያን ጦር በአዲስ አበባ ሳያበቃ ቦንብ በመወርወር ጥቃት ያደረሱበት ወጣቶች ተሸሽገውበታል ብሎ በጠረጠራቸው ቦታዎች አሰቃቂ ጥቃት ፈጽሟል።

ይህንን ቀን ለመዘከር ስድስት ኪሎ ሰማዕታት አደባባይ አባት አርበኞች በተገኙበት ዛሬ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።        

አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ በወቅቱ የ15 ዓመት ታዳጊ እንደበሩ ያጫወቱን ሲሆን በጊዜው የነበረውን እንዲህ ያስረዳሉ።    

'' ግፈኛው ፋሺስት ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ወረራ አድርጎ የግፍ አገዳደል ከ 30 ሺህ ሰው በላይ ብዙሃኑን ሴት ወንድ አሮጊት ሳይል ጥይቱ ቢያልቅበት በአካፋና በዶማ የጨፈጨፈበት ቀን ነው።''  ብለዋል 

እንደ አርበኛ መኮንን ገለጻ አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ያሁሉ ፈተናና ችግር አልፏል አሁን ያለው ወጣት ግን ድህነት ለመቀነስ መስራት ነው ያለበት ሲሉ ተናግረዋል።

''አሁን ግን ወደ ልማት ለሊት ተቀን 24 ሰዓት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይባል መማር ማጥናት ከችግር እንድንወጣ  ከብድር እንድንወጣ  ስንዴ ከአሜሪካ ነው የሚመጣው እንዲቀር ማድረግ ነው አሁንም ይህ እየተደረገ ነው።''  ብለዋል፡፡ 

አርበኛ ስዩሜ ተክለብርሃን በበኩላቸው ትውልዱ ታሪኩን በአግባቡ እንዲረዳ ከመንግሥትና ከአባቶችና ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።    

አሁን ትውልዱ  በታሪክ እያጠና በእውቀቱ እየተመራመረ የተሻለ ነገር ላይ ለመድረስ መጣጣር ነው ያለበት  ያሉት አርበኛ ስዩሜ ተክለብርሃን  መለያየቱን ጥሎ  መናናቁን ጥሎ ተከባብሮ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሌላው ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ  እጅ ለእጅ ተያይዞ አገሩን ማሳደግ ነው ያለበት  ብለዋል 

''ወጣቱ ወኔ የሚሆነው ጠይቆ ተረድቶ እኛንም በጥሩ ሁኔታ በትክከለኛ የሰማነውን ተናግረን እነሱም የሰሙትን ጽፈው አስቀምጠው ታሪኩን ለትውልድ ለሚመጣው ማስተላለፍ እንዳለባቸው ነው።''የአባት አርበኛ ልጅ ታከለ ፊጡማ ነው

ቀኑን ምክንያት በማደረገ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበርና የመንግሥት ተወካዮች ለተሰዉ ሰማዕታት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም