የአድዋ ድል በዓል ሲከበር- ቃል ይገባል የመሠረት ድንጋይ ይቀመጣል- ምንም አይፈጸምም-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል በዓል ሲከበር- ቃል ይገባል የመሠረት ድንጋይ ይቀመጣል- ምንም አይፈጸምም-ነዋሪዎች
አክሱም የካቲት 12/2011 የአድዋ ጦርነት የተካሄደባቸውን ታሪካዊ ሥፍራዎች ለማልማት የሚገባው ቃልና የተቀመጡ የመሠረት ድንጋዮች ወደ ግንባታ አለመለወጣቸ የከተማው ነዋሪዎች ቅሬታቸው ገለፁ።
የከተማዋ ከንቲባ ዘንድሮም ''ተጨማሪ የመሠረት ድንጋይ እንጠብቃለን'' ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በከተማዋ የጦርነት ታሪክ የተመዘገበባቸውን ሥፍራዎች ለኢኮቱሪዝም ልማት ለማዋል በከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚገባው ቃል አይፈጸምም፤የመሠረተ ድንጋዮችም ባሉበት ዓመታትን አስቆጥረዋል።
በከተማዋ የአብነት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ግደይ አጽብሃ ከተማዋ በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ የድንቅ ታሪክ ባለቤት ብትሆንም፤ ታሪኳን የሚመጥን የልማት ሥራዎች እስካሁን እንዳልተሰራላት ይገልጻሉ።
በተለይ የጣልያን ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያውያን የተባበረ ሽንፈት የተከናነበበት በዓል በየዓመቱ ሲከበር በፌዴራል መንግሥት በከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሚገባው ቃል የዘለለ ነገር አላየሁም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ገድል የፈጸሙባቸው የጦርነት አውድማዎች ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የመሠረተ ልማት ተቋማት እንደሚዘረጉ የተገለጸው በቀድሞው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት እንደነበር አስታውሰዋል።
በሥፍራው ሙዚዬም ለመገንባት የተያዘው ፕሮጀክት ከቃል አለማለፉ ያሳዝናል ያሉት በከተማዋ የሓየሎም ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዛፉ ሙላው ናቸው ።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ገብረመድህን ተስፋይ በበኩላቸው በከተማዋ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በየዓመቱ ቃል መግባትና የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ''እየተለመደ የመጣ በሽታ ሆኗል” ብለዋል።
የአድዋ ከተማ ከንቲባ ዘስላሴ ዘርዓብሩክ በከተማው ወራሪውን የጣልያን ጦር ኃይል ድል የተመታባቸውን የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችን ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል በየጊዜው ቃል ይገባል እንጂ፤ ሲፈጸም እንዳላዩ ይናገራሉ።
በበዓሉ አጋጣሚ ቃል ከተገቡ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የምንድብድብ ዘመናዊ ሙዚዬም፣የሰሎዳ ተራራና አካባቢ የኢኮ ቱሪዝም ልማትና የፖን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ እንደሚገኙባቸውም አስታውሰዋል።
የቀድሞው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 200ሚሊዮን ብር እንደሚመደብ የገለጹት ባለፈው ዓመት እንደነበርም አመልክተዋል።
በየጊዜው የተገባውን ቃልና የመሠረት ድንጋዮቹን ጉዳይ ለመከታተል ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ምላሹ ''የተለመደው ዝምታ ነው'' ብለዋል።
ዘንድሮ ለ123ኛ ጊዜ በሚከበረው የአድዋ ድል በዓልም ''ሌላ ተጨማሪ የመሠረት ድንጋይ እንጠብቃለን'' ብለዋል።
የአድዋ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ጽጌ ተክለማርያም በበኩላቸው በጀት ሳይኖር ማቀድና የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ተገቢ ያለመሆኑን ይናገራሉ።
የአድዋ ድልን ለማክበር ባለፉት 24 ዓመታት ለአምስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋዮች መቀመጣቸውን አስታውሰዋል።