ለህዳሴው ግድብ ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር የተገናኙ ስራዎችን ለማከናወን ከቻይና ኩባንያ ጋር ውል ተገባ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴው ግድብ ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር የተገናኙ ስራዎችን ለማከናወን ከቻይና ኩባንያ ጋር ውል ተገባ
አዲስ አበባ የካቲት 11/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር የተገናኙ ስራዎችን ለማከናወን ጌዡባ ግሩፕ (ሲጂጂሲ) ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር የውል ማሻሻያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል።
የፊርማ ስነ-ስርዓቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ እና በኢትዮጵያ የሲጂጂሲ ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ያንግ ኪያን ተፈራርመዋል።
ከኩባንያው ጋር የተካሄደው ስምምነት የ40 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደረስ ወጪ አንደሚፈጅ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኮንትራት ስምምነቱ ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር የተገናኙ የብረታ ብረት ስራዎች ፣ የውሃ ማስተንፈሻ ፣ የውሃ ማቀቢያ ፣ ከውሃ መቀልበሻ ጋር በተገናኘ ሙሉ የተጓደሉ እቃዎችን በማቅረብ፣ የጥራትና የልኬት ችግር ያለባቸውን በማስተካከል፣ በማምረት እና የተከላ ስራዎችን እንዲሁም ከዚሁ ጋር የተያያዙ የመቆጣጠሪያ በሮችን ስራ እንደሚያጠቃልል በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ዶክተር አብርሃም በላይ በዚሁ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራን ለማፋጠን ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ስምምነቶች መካሄዳቸውንና ይህ ስምምነትም የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማፋጠን ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱን ግንባታ በተቀመጠለት መርሃ ግብር መሰረት ለማጠናቀቅ ፕሮጀክቱ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ሌት ተቀን በርትተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
የሲጂጂሲ ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ያንግ በበኩላቸው ኩባንያቸው በስምምነቱ መሰረት የፕሮጀክቱን ስራ በጥራትና በተቀመጠው ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ኩባንያው በኢትዮጵያ በተለያዩ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ እንደነበረው አስታውሰዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ከዚህ በፊት ከብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የቅድመ ኃይል ማመንጫ የብረታ ብረት ስራዎችን ለማከናወን ስምምነት እንደነበረ ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት ከዚህ በፊት የነበረውን ውል በማሻሻል ስምምነት እንደተካሄደ አመልክተዋል።
ከቻይናው የስራ ተቋራጭ ጋር የተደረገው ስምምነት የፕሮጀክቱ ወሳኝ ስራ አካል እንደሆነም ኢንጂነር ክፍሌ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች እና ሌሎች ከፍተኛ የኃይል ማሰራጫዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያስችሉና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን ቮይት ሀይድሮ ሻንጋይ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
ይህ ስምምነት ከግድብ፣ ከማስተንፈሻ፣ ከሳድል ዳም እና ከሌሎችም ጋር ሁሉንም የሚያገናኙ ስራዎችን ለማከናወን እንደተካሄደ ኢንጂነር ክፍሌ ገልጸዋል።
የፊርማ ስነ ስርዓቱንም ዶክተር አብረሃም በላይ እና የቮይት ሀይድሮ ሻንጋይ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ታንግ ሹ የተፈራረሙ ሲሆን ከኩባንያ ጋር የተካሄደው ስምምነት የ113 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይል መረጃ ያሳያል።
በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት የነበረው ግድቡ ሳይጠናቀቅ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል።
በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አማካኝነት መሰራት የነበረበት የግድቡ ኤሌክትሮ ሜካኒካልና ተያያዥ ተግባራት አፈፃፀም በመጓተቱ ነው ስራውን በተያዘው ጊዜ ማጠናቀቅ ያልተቻለው።
በዚህም የተነሳ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ አራት ዓመታት አስፈልጓል።
የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በተለይ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ቀደም ሲል የነበረው ጉድለት እንዳይደገምና ግድቡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥራት እንዲኖረው የሚያስችሉ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ከሳምንት በፊት አስታወቀዋል።
ፕሮጀክቱን በተያዘው ጊዜና በሚፈለገው ጥራት ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።