ቀጥታ፡

ሳሳካዋ ግሎባል ባለፉት 25 ዓመታት በግብርናው መስክ ኢትዮጵያን ደግፏል---- ግብርና ሚኒስቴር

አዳማ የካቲት 11/2011 ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ባለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና አሁን ለደረሰበት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሀገሪቱን ግብርና በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታና በተቀናጀ ኤክስቴንሽን ለማጠናከር የሚረዳ ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀቱን ሳሳካዋ ግሎባል 2000 አስታውቋል።

ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽንና ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ ያዘጋጁት የ3 ቀናት የምክክር መድረክ ዛሬ ተጀምሯል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ከግብርና አመራሮች፣ ከባለሙያዎች፣ ከአርሶ አደሮችና በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በቅርበት በመስራት ለግብርናው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ እንቅስቃሴን ለማጠናከርና ከምርት እስከ ግብይት ድረስ ያለውን የእሴት ሰንሰለት ለማዘመን ያደረገው ድጋፍ መኖሩንም አመልክተዋል።

መንግስት የግብርናው ዘርፍ የበለጠ ለማዘመንና ከኢንዱስትሪው ጋር ያለው ተመጋጋቢነት ለማጠናከር አዲስ ስትራቴጂክ እቅድ እያዘጋጀ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በእዚህ ወቅት ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ከሚገኝበት ደረጃ ጋር የሚጣጣም የራሱ የሆነ የአምስት ዓመት ስትራተጂክ ዕቅድ ማሰናዳቱ ተገቢና ወቅታዊ  በመሆኑ እንደሚደገፍ አመልክተዋል።

የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን ሪጅናል ዳይሬክተር ዶክተር ሜል ኦሉኦች በምክክር መድረኩ ላይ እንደተናገሩት ሳሳካዋ ግሎባል ዛሬም እንደትናንቱ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በቅድመና ድህረ ምርት አያያዝ ፣ ገበያን ማዕከል ባደረገ አመራረት ትስስሩን ለማሻሻል ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ ይሰራል ።

የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ፋንታሁን መንግስቱ በበኩላቸው ” አሁን የተዘጋጀው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በዓመት በአማካይ እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ በጀት እንደሚመደብለትና እንደ አስፈላጊነቱ እየጨመረ የሚሄድ ነው” ብለዋል።

ይኽው አራተኛው ምዕራፍ ስትራቴጂክ እቅድ 80 ሺህ አርሶ አደሮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው በጥራት እንዲያመርቱ ፣ ለኢንዱስትሪ እንዲያቀርቡና ወደማቀነባበር እንዲሸጋገሩ ብሎም የምርት ብክነትን እንዲቀንሱ የሚያስችል ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አመልክተዋል።

ዶክተር ፋንታሁን እንዳሉት እቅዱ በሀገሪቱ  ከሚገኙ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የግብርና ትምህርትና የግብርና ኤክስቴንሽን አቅም ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡

እስካሁን ድረስም በ9ኙ ዩኒቨርሲቲዎች 1ሺህ 300 የግብርና ልማት ሠራተኞች ተመርቀው ወደነበሩበት ሥራ መመለሳቸውን አስረድተዋል ።

ዶክተር ፋንታሁን እንዳሉት በ60 ወረዳዎች ሁሉንም የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከማምረት እስከ ተጠቃሚው ድረስ የሚዘልቅ ሞዴል የእሴት ሰንሰለት የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ታቅዷል።

ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግ በበቆሎ ምርት ላይ መስራት የጀመረ ሲሆን ምርቱ አድጎ አርሶ አደሩ ገበያ በማጣቱ  ወደ እሴት ሰንሰለት በመሸጋገር ኤክስቴንሽኑን ሲደግፍ ቆይቷል።

ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረጉን የተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር አንተነህ ግርማ ተናግረዋል።

የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ አዲሱ የአምስት ዓመት ስትራተጂክ እቅድ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ፣ የክልልና የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለድረሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገበት ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም