ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ የጠየቀውን ይግባኝ አደመጠ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ የጠየቀውን ይግባኝ አደመጠ

አዲስ አበባ የካቲት 11/2011 የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መርማሪ ፖሊስ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ የጠየቀውን ይግባኝ አደመጠ።
ችሎቱ የክርክር መዝገቡን መርምሮ በይግባኙ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 13 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል።
በህግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ሶስት ወራትን የዘለሉት የቀድሞው የኢትዮ ቴሌኮም የስራ ሃላፊ አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ ጉዳያቸው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ሲታይ ቆይቶ በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ተፈቅዶላቸው ነበር።
ዋስትናውን የተቃወመው የፌዴራሉ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ይግባኙን ውድቅ አድርጓል።
ነገር ግን መርማሪ ፖሊስ ግለሰቡን በሌላ የሙስና ወንጀል ድርጊት ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል በአዲስ ምርመራ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ስለጠየቀባቸው በከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛው ወንጀል ችሎት የድርጊቱ ፍሬ ነገር ቀርቦ ነበር።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት 10ኛው ወንጀል ችሎትም የተጠርጣሪ ጠበቆችና የአመልካችን ክርክር ካደመጠ በኋላ የካቲት 8 ቀን 2011 በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲወጡ ውሳኔ ቢሰጥም በውሳኔው ቅር የተሰኘው መርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቋል።
በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተጠርጣሪንና አመልካችን ክርክር አድምጧል።
መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ እንዳስረዳው ተጠርጣሪው በኢትዮ ቴሌኮም 'ኤንጂፒኦ' የተባለ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ያለውድድርና ጨረታ ኢዲኤም የተባለ የውጭ አማካሪ ድርጅት ጋር ውል በመፈጸም መጠርጣራቸውን ገልጿል።
እንዲሁም ከ2001 እስከ 2005 ዓ.ም. ለ12 የአማካሪ ድርጅቱ ሰራተኞች ሥራ ሳይሠሩ በሰዓት ከ125 እስከ 150 ዶላር፤ ለአማካሪ ድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ደግሞ በሰዓት 150 ዶላር ካለአግባብ ክፍያ እንዲፈጸም አድርገዋል፤ ስራው ሲጠናቀቅ የሚከፈል የ10 በመቶ ክፍያም ስራው መጠናቀቁ ሳይረጋገጥ 104 ሺህ 495 ዶላር ክፍያ እንዲከፈል አድርገዋል በሚል መጠርጣራቸውን አስረድቷል።
በዚህም የወንጀል ድርጊት ለምርመራ የሚያበቃ የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡንና የአንድ የሰው ምስክር ቃል መቀበሉን በማስረዳት ነገር ግን፤ በተጠርጣሪ ላይ ክስ ለመመስረት ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ በዋስትና እንዲወጡ መወሰኑን ገልጿል።
በዚህም ግለሰቡ የተጠረጠረበት ወንጀል ከባድ የሙስና ወንጀል በመሆኑና ለምርመራ የሚያበቃ በቂ ምክንያት እያለ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲወጡ ስለወሰነ ውሳኔው ውድቅ ተደርጎ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜው እንዲፈቀድለት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት ብሏል፡፡
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ አዳዲስ የወንጀል ድርጊቶችን በማምጣት ቀጠሮ እየጠየቀ ለሶሰት ወራት ቢቆይም እስካሁን ክስ መመስረት አለመቻሉን ገልጸዋል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪ ላይ የፈቀደው የዋስትና ውሳኔም ተገቢና የፍርድ ቤቱን ገለልተኝነት፣ታማኝነት የሚያረጋግጥና የፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት የሚያስጥል ውሳኔ በመሆኑ አግባብነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
ተጠርጣሪ ለ100 ቀናት ያላግባብ መተሰራቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ስልጣኑን አላግባብ እየተጠቀመ መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፤ "በጉዳዩ ላይ የህግ ክርክር ጨርሰናል፤ የምንጠብቀው የፍርድ ቤቱን የህሊና ፍርድ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
አሁን በተጠርጣሪ ላይ ተገኘ የተባለው የወንጀል ድርጊትም መርማሪ የሚቆጣጠረው ባለመኖሩ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በሚል ሰበብ ተጠርጣሪን በየፍርድ ቤቱ ማንገላታት እንጂ ፈጽመውታል የተባለ ተጨባጭ ምክንያት አልቀረበም ሲሉ ይግባኙን ተቃውመዋል።
ግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ፤ከዚህ በፊት የተደረጉ ክርክሮችን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጥዋት ላይ ቀጠሮ ሰጥቷል።