ቀጥታ፡

የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመሟላትና ቀልጣፋ የአገልግሎት እጥረት የኢንቨስትመንቱ ማነቆዎች መሆናቸውን ባለኃብቶች ገለፁ

አዲስ አበባ  የካቲት 11/2011 የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመሟላትና ቀልጣፋ የአገልግሎት እጥረት የኢንቨሰትመንት ዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውን ባለኃብቶች ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዛሬ ከባለኃብቶች ጋር ባካሄደው ስብሰባ ከዘርፉ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በዚሁ ወቅት ባለኃብቶቹ እንደገለጹት የከተማው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ዝቅተኛ በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን በጥራትና በፍጥነት ማግኘት አልተቻለም።

በዚህም የተነሳ ዘርፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ረጅም ጊዜ መጠበቅ፣ የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ፣ የመሬትና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት ዘርፉ ከተጋረጡበት ችግሮች መካከል መሆናቸውን ባለኃብቶቹ ገልፀዋል።

በተለያየ የኢንቨስትመንት መስኮች ለተሰማሩ የአገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች በቂ ድጋፍ አለማድረግና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ተብሎ በሚተገበረው ከቀረጥ ነጻ  ማበረታቻ ስርዓት ላይ ያሉ ክፍተቶች ሌሎቹ የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውም ተመልክቷል።

መንግስት ከአገር ውስጥ ባለኃብቶች ይልቅ ለውጭ ባለኃብቶች የተለየ ድጋፍ ማደረጉ ላይም ተሳታፊዎቹ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

በእነዚህም ችግሮች ሳቢያ በስራቸው ውጤታማ ለመሆን እንዳልቻሉ ነው ባለኃብቶቹ ያመለከቱት።

የመሰረተ ልማት አቅርቦት ማሟላትንና ቀልጣፋ አገልግሎት ስርዓት መዘረጋትን ጨምሮ የተጠቀሱት የአሰራር ክፍተቶች እንዲስተካከሉ  ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አየተገኘ አይደለም ሲሉ ነው የውይይቱ ተሳታፊ ባለኃብቶች የተናገሩት። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ "የተነሱትን ችግሮች ለመፍታት ከፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በጋራ እንሰራለን"  ሲሉ ቃል ገብተዋል።

በአሁኑ ወቅት እየቀረበ ላለው እያንዳንዱ የመሬት ጥያቄ  ምላሽ ለመስጠት አይቻልም ያሉት ኮሚሽነሩ የባለ ኃብቶችን የመሬት አቅርቦት ለማሟላት ግን ከመዲናዋ አስተዳደር ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት መሬት ለሚፈልጉ ባለኃብቶች 93 ሄክታር የሚደረስ መሬት በኪራይ መልክ ማቅረብ በሚቻልበት መንገድ ላይ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀዋል።

ይህ የመሬት አቅርቦት መጠን በአሁኑ ወቅት መሬት ለማግኘተ አየተጠባበቁ ካሉት ባለኃብቶች ቁጥረ አንፃር እጀግ አነስተኛ ቢሆንም የመሬት ጥያቄ አቅርበው ረጅም ጊዜ እየጠበቁ ለሚገኙ ባለኃብቶች ምላሽ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል። 

ከኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ የኢንቨስትመንት ዘርፉ እየገጠመው ያለውን ችግር ለመፍታት አንድ ቡድን የተቋቋመ  ሲሆን ወደ ስራ ለመግባት ሂደት ላይ ነው ብለዋል። 

የቀረጥ ነጻን ጨምሮ ዘርፉን ለማበረታታት ተብለው የተቀየሱት አሰራሮችን ከተፈቀደው ዓላማ ውጭ ተገቢ ባልሆነ መልኩ ጥቅም ላይ የሚያውሉ አካላት መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ አብዱልፈታህ ይህንን ለመከላከል በጉምሩክ በኩል በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለኃብቶችም የዚህ ዓይነት ህገ ወጥ ተግባርን ሲታዘቡ ጥቆማ በመስጠት በጋራ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

ለውጭ ባለኃብቶች ቅድሚያ የሚሰጠው በአገሪቱ የሚታየን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያቃልላሉ በሚል እምነት መሆኑንም የከተማው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አብራርተዋል።

ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋርም በጋራ የሚሰሩ ስራዎችን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው "ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል።

አቶ አብዱልፈታህ እንደተናገሩት የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ይህም በርካታ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም