የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላኪዎች የተሳተፉበት 24ኛው የገልፍ ፉድ ኤግዚቢሽን እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላኪዎች የተሳተፉበት 24ኛው የገልፍ ፉድ ኤግዚቢሽን እየተካሄደ ነው
ዱባይ የካቲት 11/2011 የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላኪዎች የተሳተፉበት 24ኛው የገልፍ ፉድ ኤግዚቢሽን እየተካሄደ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በኤግዚቢሽኑ ላይ የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች ማሳያ (ፓቪሊዮን) በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋና በዱባይና በሰሜን ኤሜሬቶች በዱባይ ቆንስላ ጄኔራል ወይዘሮ እየሩሳሌም አምደማሪያም ተከፍቷል።
ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በምግብ ምርቶች ላይ የሚያተኩረው የ'ገልፍ ፉድ ኤግዚቢሽን' ከየካቲት 10 እስከ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በዱባይ ይካሄዳል።
በዱባይ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ማዕከል በሚካሄደው ''በ24ኛው የገልፍ ፉድ 2019 ኤግዚቢሽን'' ላይ ከ187 በላይ አገሮች የወጪ ምርቶች ላኪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በኤግዚቢሽኑ 63 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽያጭ ይከናወንበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በፕሮግራሙ የቡና፣ የስጋ፣ የቅባት እህሎች ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ የእንስሳትና የማር ምርቶች መቅረባቸውን ያመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ''የአገራችንን የቱሪዝም ሀብቶች ባህላዊ ምግቦችና የቡና አፈላል ስነ-ስርዓት የሚያስተዋውቅ ፕሮግራም ቀርቧል'' ብሏል።
ኤግዚቢሽኑ ለኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር እንደታመነበት ሚኒስቴሩ አመልክቷል።