ከፍተኛው ፍርድ ቤት የአቃቤ ሕግን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛው ፍርድ ቤት የአቃቤ ሕግን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጠ
አዲስ አበባ የካቲት 11/6/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢምፔሪያልና ሪቬራ ሆቴሎችን ግዥ አስመልክቶ አቃቤ ሕግ ያቀረበውን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።
የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ላይ የኢምፔሪያልና ሪቬራ ሆቴሎችን ግዥና ሽያጭ አስመልክቶ በመዝገብ ቁጥር 229498 ክስ መመስረቱ ይታወቃል።
በዚህ የክስ መዝገብ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኝው፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል፣ ብርጋዴር ጄኔራል በርሃ በየነ፣ አቶ አለም ፍጹም፣ ሌተናል ኮሎኔል አስመረት ኪዳኔ፣ ሌተናል ኮሎኔል ግርማ መንዘርጊያ፣ ሻምበል አግዘው አልታዬና አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ይገኙበታል።
አቃቤ ሕግ ዛሬ ተከሳሾቹ ስለ ክሱ ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ያቀረቡትን መቃወሚያ መሰረት አድርጎ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት የመጀመሪያ ዙር ዝርዝር ምላሽ ሰጥቷል።
ተከሳሾቹ ያቀረቡት መቃወሚያ ወደፊት ማስረጃ በማሰማት ሒደት የሚጣራ በመሆኑ አግባብነት እንደሌለው ነው በምላሹ ያተተው።
ፍርድ ቤቱም አቃቤ ሕግ በጽሑፍ ያቀረበውን የመጀመሪያ ዙር ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።