በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ መሪ ሆነ

አዲስ አበባ የካቲት 11/2011 በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሪነቱን ተረክቧል ።

በኢትዮጵያ የወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የምድብ አንድ ቀጣይ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ተደርገዋል።

በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ተካሄደዋል።

ከትናንት በስቲያ ዱራሜ ላይ በተደረገ ጨዋታ ከምባታ ዱራሜ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ 28 ለ 28 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ትናንት ጎንደር ላይ በተደረገ ጨዋታ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ጎንደር ከተማን 31 ለ 21 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ነጥቡን 12 በማድረስ የሊጉን መሪነት ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተረከበ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥብ  በመጣሉ ምክንያት በ11 ነጥብ ወደ ሁለተኛ ዝቅ ብሏል።።

ኮልፌ ቀራንዮ በሊጉ እስካሁን ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎችም በማሸነፍ ውጤታማ ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥብ የጣለው ከአምስት ተከታታይ ጨዋታ አሸናፊነት በኋላ ነው።

ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መከላከያ ቡታጅራ ከተማን አስተናግዶ 29 ለ 19 አሸንፏል።

ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከድሬዳዋ ከተማ ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ጨዋታ እንዲያደርጉ መርሃ ግብር ቢወጣላቸውም ድሬዳዋ ከተማ የማራዘሚያ ጥያቄ በማቅረቡ ጨዋታው አለመካሄዱን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስነ ስርአት ኮሚቴ ጨዋታው መቼ መካሄድ እንዳለበት ለመወሰን ነገ ስብሰባ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

በዚህ ሳምንት መቐለ ሰብዓ እንደርታና ፌዴራል ፖሊስ ጨዋታቸውን የማያደርጉ በመሆናቸው እረፍት የወሰዱ ቡድኖች እንደነበሩ ይታወቃል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የምድብ አንድ ቀጣይ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ሲካሄዱ ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ሀዋሳ ከተማን 54 ለ 52፣ ትናንት ደግሞ ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን 77 ለ 45 አሸንፏል።

በዚሁ ምድብ አርብ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት አዳማ ከተማን 68 ለ 35 ማሸነፉ ይታወሳል።

በ2011 ዓ.ም ቡድኖች በሁለቱም ጾታዎች በሁለት ምድብ ተከፍለው በዙር ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል አዲስ አሰራር መዘርጋቱን ተከትሎ ቡድኖች በምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።

በዚሁ መሰረት በወንዶች ፕሪሚየር ሊግ በምድብ አንድ የተደለደሉት ሶስቱ ክለቦች ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በእርሳቸው ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በወንዶችና በሴቶች የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በተመሳሳይ በምድብ ሁለት የሚገኙት ቡድኖች በዚህ ሳምንት በጎንደር ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን መግለጹ የሚታወስ ነው።

በዚሁ መሰረት የተራዘሙት ጨዋታዎች በተያዘው ሳምንት መጨረሻ እንደሚካሄዱ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

በተጨማሪም ትናንት በሰባተኛ ሳምንት በሀባሻ ሲሚንቶ የወንዶች የቮሊቦል የፕሪሚየር ሊግ በተካሄደ አንድ ጨዋታ ባህርዳር ጣና ሙገር ሲሚንቶን በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም