ቀጥታ፡

የከተሞች ፎረም በግንባታው ዘርፍ ያሉትን ችግሮች ለመከላከል የሚያስችል መልካም እድል ይፈጥራል - በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት

ጅግጅጋ ጥር 11/2011 በኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም በየዓመቱ መካሄዱ በግንባታው ዘርፍ ያሉትን ችግሮች ለመከላከል የሚያስችል መልካም እድል እንደሚፈጥር በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ገለፁ።

“መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ጅግጂጋ እያስተናገደችው በሚገኘው ብሄራዊ የከተሞች ፎረም ላይ ከ168 በላይ የአገሪቱ ከተሞች ተሳትፈዋል።

በኢትዮጵያ የጋራ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ ለተለያየ አገልግሎት ተብለው በከተሞች የሚገነቡ ህንፃዎች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል የጊዜና የኃብት ብክነት  አንደዚሁም  የዲዛይን ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል።

ይህም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዳይበቁ እና ከፍተኛ የጥራት ጉድለት እንዲገጥማቸው ከማድረግ ባሻገር በአጠቃላይ የግንባታ ፕሮጀክቶች ወጪ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።

በኢትዮጵያ ከከተማ ልማት ጋር በተያያዘ ያሉ መሰል ችግሮች ለመከላከል የከተሞች ፎረም ልምድ፣ ቴክኖሎጂና አሰራር ለመዘርጋት ያግዛል ሲሉ ነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አሻ ለኢዜአ የገለፁት።

ከተሞች በደረሱበትና ባላቸው የግንባታ ቴክኖሎጂ እንዲወዳደሩ ለማድረግም ዓመታዊው የከተሞች ፎረም ዓይነተኛ መሳሪያ ሊሆን ይችላል በማለትም አክለዋል። 

እንዲሁም ከተሞች በአገር ውስጥና ከውጭ አገራት ያለን ልምድና ተሞክሮ እንዲቀስሙ እንደሚያስችላቸውም ገልፀዋል። 

እንደ ዶክተር አርጋው ማብራሪያ በከተሞች ፎረም ከተሞች ያላቸውን ቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን በሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሁፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ቴክኖሎጂዎች እንዲያውቁ ይረዳቸዋል።

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገኦ በበኩላቸው በየዓመቱ የሚካሄደው የከተሞች ፎረም በዘርፉ ያለቱን በርካታ ችግሮች ለይቶና ቅድሚያ ሰጥቶ ለመፍታት እንደ ግብዓት የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

ከፎረሙ የሚገኙ ልምዶች በግንባታዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ጠቅሰው በተለይም ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውን ከተሞች ለማበረታታት ይረዳል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ከመኖሪያ ቤት እስከ ኢንዱስትሪ ፓርክ ድረስ ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን የከተሞች ፎረም መዘጋጀቱ በትላልቅ ከተሞች በሚካሄዱ ግንባታዎች ላይ የሚያጋጥሙ የዲዛይን፣ የፍሳሽ አወጋገድና መሰል ችግሮችን ለማረም አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

የከተሞች ፎረም በጅግጅጋ ከተማ ካለፈው መጋቢት 9 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም