መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር ሊተጉ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር ሊተጉ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ የካቲት 11/2011 መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን ጠንቅቆ በማወቅ ለማክበርና ለማስከበር ሊተጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ።
"የሰብአዊ መብት ከማክበርና ከማስከበር አንፃር የፖሊስ ሚና" በሚል ኮሚሽኑ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል።
ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ ለመጪዎቹ 11 ቀናት በሰባት ዙር የሚካሄድ ሲሆን ከ1 ሺህ 500 በላይ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተውጣጡ ፖሊስ አባላት ይሳተፋሉ።
የመጀመሪያው ዙር ስልጠና ዛሬ ሲጀመር የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር ሁሉም ተቋማት የተቋቋሙት ከመብት ጋር ቁርኝት ያላቸውን የሰው ልጅን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለማክበርና ለማስከበር ነው ብለዋል።
ስለዚህም ሰብአዊ መብትን ማክበርና ማስከበር የኮሚሽኑ ተግባር ብቻ ባለመሆኑ የመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የጋራ አጀንዳ የሆነውን የሰብአዊ መብት ጉዳይ በማወቅ ለማክበርና ለማስከበር መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብት ሰራዊት ለመገንባት የግንዛቤ ማሳደጊያ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገለጸው በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ወቅታዊና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
በሰብአዊ መብት ዙሪያ የምርመራና ክትትል ስራ በማከናወንና ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑትን የኀብረተሰብ ክፍሎች መብቶች ለማክበርና ለማስከበር በርካታ ስራዎች ሲያከናውን መቆየቱንም አብራርተዋል።
ግንዛቤ የማስፋት ስራ አካል የሆነውና ለፖሊስ አባላት የሚሰጠው ስልጠና በሰብአዊ መብት ፅንሰ ሃሳብና ዳራ፣ በተጠርጣሪዎች አያያዝና የምርመራ ሂደት፣ የህግ አስከባሪዎች ስልጣንና ተግባር እንዲሁም ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች መብቶች ላይ የሚያተኩር ነው።
ስልጠናው በቂርቆስ ክፍለከተማ ፖሊስ መምሪያ ስር ላሉ አምስት የስራ ክፍሎችና ስድስት ፖሊስ ጣቢያዎች ለተውጣጡ አመራርና አባላት የሚሰጥ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የፖሊስ መምሪያው የሰው ሃብት ልማት አስተዳደር ኃላፊ ኮማንደር አይናለም መንገሻ ናቸው።