የምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከአህጉሪቷ ክፍለ ኢኮኖሚዎች የተሻለ ነው-የአፍሪካ ልማት ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከአህጉሪቷ ክፍለ ኢኮኖሚዎች የተሻለ ነው-የአፍሪካ ልማት ባንክ
አዲስ አበባ የካቲት 10/2011 ባለፈው የፈረንጆች 2018 ዓመት የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የምጣኔ ሀብት በአህጉሪቱ ካሉ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ጠንካራ እንደነበረ የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዋና ዳይሬክተር ገለጹ።
በቀጣናው ባሉ አገሮች የተመዘገበው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ጠንካራ፣ የተለየና ግልጽ ስርዓት እንዳለውም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብርኤል ንጋቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ቀጣናው መጠነኛ የመሠረታዊ መብት ጥያቄዎች የሚነሱበት አካባቢ ቢሆንም የተመዘገበው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ጠንካራ በመሆኑ ዕድገቱ በተያዘው የፈረንጆች 2019 ዓመት እንደሚቀጥል ይገመታል።
ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ከምስራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግባለች።
በዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ግን ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገሮች በስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የድርጅቱ ሪፖርት ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተግዳሮት ያለበት እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መንግስት በምጣኔ ሀብቱ ላይ ትልቅ ማሻሻያ እያደረገ በመሆኑ አጠቃላይ ዕድገቱ የሚያበረታታ እንደሆነም ነው አቶ ገብርኤል የሚናገሩት።
እንደ አቶ ገብርኤል ማብራሪያ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተነጻጻሪ ዕድል ያላት አገር በመሆኗ በዘርፉ ላይ ትኩረት አድርጋ የሚታካሄደው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታም ዘርፉን ለማሳደግ ጠቃሚ ነው።
ባንኩ ለአራት አዳዲስ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ድጋፍ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህም የግብርና ምርቶችን ከአግሮ ኢንዱስትሪው ጋር በማገናኘት ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ተደርጓል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ሥራ ፈላጊ ወጣት ሲሆን መንግስት በአገሪቱ ያለውን የሥራ አጥ ችግር ለመፍታት የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ማቋቋሙም ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ ነው አቶ ገብርኤል ያወሱት።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋር መሆኑን የገለጹት አቶ ገብርኤል በቅርቡ የባንኩ ፕሬዝዳንት ሚስተር አኪንውሚ አዴሲና ኢትዮጵያ ቅድሚያ በሰጠቻቸው ስድስት ዘርፎች ላይ ባንኩ ድጋፍ በሚያደርግበት ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ባንኩ ለአራት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ድረስ ያለው የመንገድ ጥገናና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሁም በሰው ኃይል ልማት የኢትዮጵያ መንግስት ለነደፋቸው ስትራቴጂዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ለምታስገነባቸው ለአራት አዳዲስ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ አንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሲጠናቀቅ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎም ይገመታል።