ቀጥታ፡

በምስራቅ ሃረርጌ ግምታቸው 5 ሚሊዮን ብር የሆነ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

ሀረር የካቲት10/2011 ግምታቸው አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው  የኮምንኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን ሃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፋ  ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አቃዎቹ ከቶጎ ውጫሌ አቆራርጠው ወደ መሀል አገር ሊገቡ ሲል በዞኑ ጭናክሰን ወረዳ ላይ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የካቲት 9/2011 ዓ.ም. ንጋት ላይ የወረዳው አድማ ብተና እና መደበኛ የፖሊስ አባላት ባደረጉት የኦፕሬሽን ስምሪት ኮድ 3- 04878 ድሬ፣ ኮድ 3-04677 ሶ/ማ እና ኮድ 3- 59728 አ/አ የሆኑ ሶስት አይሱዙ የጭነት መኪናዎች 5 ሚሊዮን ብር ከሚገመት እቃዎች ጋር ተይዘዋል።

ከኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል ቴሌቭዥን፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ፣ ማቀዝቀዣ ፣ ፍሪጆች ፣ የተለያዩ የሞባይል ቀፎዎችና ባትሪዎች፣የተለያዩ አዳዲስና ልባሽ ጨርቆች፣ራዲዮኖች እንደሚገኙባቸው ኃላፊው ገልጸዋል።

እንዲሁም የተለያዩ ህገ-ወጥ መዲሃኒቶች፣የመኪና መለዋወጫዎች፣የምግብ ዘይቶችና ሌሎች ቁሳቁሶችና ሶስት እሰታር ሽጉጦች ከትናንሽ ቴፕ ሪከርደሮች ጋር መገኘታቸውን ተናግረዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች በድሬዳዋ ገቢዋችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሐረር ኮንትሮባንድ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ገቢ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ኮንትሮባንዱን የጫኑት አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪዎቹን እስከ ንብረቱ ጥለው መሰወራቸውን የገለጹት ኮማንደር ስዩም የወረዳው የፖሊስ ኃይል በቁጥጥር ስር ለማዋልና ለሀግ ለማቅረብ ከህብረተሰቡ ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም