ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናና ስሟ እንድትመለስ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል- ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2010 ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናና ስሟ እንድትመለስ ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ አገሪቱን እንዲያለማ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጥሪ አቀረቡ። 77ኛው የድል በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የአርበኞች መታሰቢያ ሃውልት፤ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ አምባሳደሮችና አታሼዎች፣ ጀግኖች አርበኞች አባቶችን ጨምሮ የመዲናዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያዊያን በቆመው የአርበኞች መታሰቢያ ሃውልት ስር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ አርበኞቻችን የዛሬ ሰባ ዓመት በቂም በቀል ስሜት ተነሳስቶ አገሪቱን በድጋሚ ለመውረር የመጣውን የፋሺስት ጦር ባዶ ህልሙ እንዲመክን ያደረጉበት በዓል ነው ብለዋል። የኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ድል የሰሙና ሌሎች በቅኝ ገዢዎች ስር ለነበሩ ጥቁር ህዝቦች ከፍተኛ የሞራል ኃይል እንደሆናቸው የገለፁት ፕሬዝዳንቱ የተደራጀ ትጥቅ የታጠቀውን ወራሪ ኃይል ሽንፈትና ኪሳራ በማከናነብ ለዓለም ህዝብ ጀግንነታችንን ያሳየንበት ነውም ብለዋል። በተለያየ ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮችን በኢትዮጵያዊነት አንድነት መንፈስ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች በነፃነት ታፍራና ተከብራ የምትኖር አገር እንድትኖር አድርጓል። አባቶቻችንና እናቶቻችን የፈፀሙትን ገድል የበለጠ እንዲደምቅ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞች የሞት ሽረት ትግል አድርገው ወራሪውን ጦር ከአምስት ዓመት መራር ትግል በኋላ ድል በማድረግ ያስገኙት ውጤት ለጥቁር ህዝቦች አንጸባራቂ ነው። በዓሉ ለቀጣይ ትውልድ መልካም አርዓያ ሆኖ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት የመንግስትና የህዝብ መሆኑን ልጅ ዳንኤል ገልጸዋል። በበዓሉ ላይ ከተገኙት ዜጎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አባት እና እናት አርበኞች፤ አርበኞች ሰማዕት ሆነው ለትውልድ ያስረከቡትን ሃገር ወጣቱ ትውልድ ሰላሟን በማስጠበቅ እና ድህነትን በመዋጋት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ጣሊያን የአድዋን ድል ለመበቀል በሚል በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤኒቶ ሙሶሎኒ አማካኝነት ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን መውረሯ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያውያንም ወራሪውን ሀይል ለአምስት ዓመታት በጽናት ታግለው 1933 ዓ.ም ድል ነስተውታል። የወቅቱ አርበኞች ለሀገራቸው ነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያስገኙትን ድል ለማሰብም በየአመቱ ሚያዚያ 27 የድል በዓል ተከብሮ ይውላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም