ሰላምን በመስበክ ሀገራዊ ለውጡን ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በመስበክ ሀገራዊ ለውጡን ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ
ደሴ የካቲት 10/2011 የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ለህብረተሰቡ ስለሰላም በመስበክ ለሀገራዊ ለውጡ ቀጣይነት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤትክርስቲያን በአገራዊ አንድነትና ሰላም ዙሪያ ከየካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀን በደሴ ከተማ ያዘጋጀችው የውይይት መድረክ ትላንት ተጠናቋል ።
በቤተክርሲቲያኗ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከት ወንጌል አገልጋይ መጋቤ ሃዲስ ሚስጥረ ስላሴ ማናዬ በወቅቱ እንዳሉት የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች ለሰላም መስፈንና ለህዝቦች አንድነት ግንባር ቀደም ሆነው መስራት ይገባቸዋል።
ልዩነቶችን በመቻቻል እንዲፈቱ ከማድረግ ባለፈ የጥንት ኢትዮጵያ ባህሎችና እሴቶች ሳይሸረሸሩ በማስቀጠል የወጣቱን ተስፋ ማለምለም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
"ማንኛውም ሃይማኖት ግድያንና ሁከትን አያስተምርም፤ ሁሉም አባት ደግሞ ልጆቹንና ወጣቱን በየእምነቱ መንፈሳዊ ህይወትንና ሰላምን ማስተማር አለበት" ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያኗም ሀገራዊ አንድነትና መግባባትን ለመፍጠር በሀገሪቱ በሚገኙ 52 ሀገረ ስብከቶች የሰላምና የአንድነት ጥሪ እያደረገች መሆኗን ጠቁመዋል።
ከታህሳስ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በ25 ከተሞች ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት አባቶችንና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በሰላም ፋይዳና በሁከትን አስከፊነት ዙሪያ በተደረገ ውይይት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በበኩላቸው ምዕምናን ከሁሉም ሃይማኖት አባቶች ጋር በመወያየት የአካባቢያቸውን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
"በሚካሄዱ ጉባኤዎች የችግሮችን መንስኤ በመለየትና እርቀ ሰላም በማውረድ የኢትዮጵያዊነት የሽምግልና ባህልን ማስጠበቅ ይገባል" ብለዋል ።
"ያለ ሰላም የሚፈጸም ተግባር ባለመኖሩ አጥፊዎችን በመምከር የአገርን አንድነት ማስቀጠል ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል ።
የመቅደላ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ እስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ዋለልኝ አዳሙ በበኩላቸው "ሀገራችን ለተለያዩ ስጋቶች የምትጋለጠው በመንግስት፣ በሃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች ቁርጠኝነት ማነስ ነው" ብለዋል ፡፡
" በተለይ የሃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም፣ አንድነትንና አብሮነት ሳንሰለች ልንሰብክ ይገባናል" ሲሉም ገልጸዋል።
በየወረዳው ያሉ የሃይማኖት አባቶችንና የፀጥታ ኃይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አማካሪ አቶ እጅጉ መላኬ ናቸው።
እንደአማካሪው ገለጻ የኢትዮጵያዊነት የሽምግልና እርቅ ስርዓትን በማጎልበት ነባር የህዝቡን ባህልና ትውፊት ለመመለስ የሁሉም ጥረት ያስፈልጋል ።
የሰላምና የአንድነት ምክክር መድረኩ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በደሴ ከተማ የተካሄድ ሲሆን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ተጠናቋል፡፡