ቀጥታ፡

የጫት መሬትን በቋሚ ተክሎችና ሰብል ማልማት እንደጀመሩ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ

ጎንደር የካቲት 10/2011 ላለፉት ስምንት ዓመታት ጫት ሲያለሙበት በነበረው መሬት ቋሚ ተክሎችንና ሰብል ማልማት መጀመራቸውን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ጫት አልሚ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡    

በዚህ ዓመት ከ70 በላይ ለሚሆኑ ጫት አልሚ አርሶአደሮች ስልጠና በመስጠት የጫት መሬታቸውን በአትክልትና ፍራፍሬ ተክተው እንዲያለሙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በወረዳው የሰርባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ጌታቸው ወርቁ  "ጫት በገቢ ደረጃ ጥቅም ቢኖረውም የወጣቱን አእምሮ በማደንዘዝ ጉዳት እንዳለው በመገንዘቤ ዘንድሮ ማልማቱን አቁሚያለሁ" ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት ላለፉት አራት ዓመታት ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን ለግለሰብ ጫት አልሚ በዓመት 4 ሺህ ብር ቢያከራዩም ዘንድሮ ግን ማንጎና አቡካዶ ለማልማት የኪራይ ውላቸውን አቋርጠዋል፡፡

በወረዳው የሳር ውሃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጎበዜ ማሞ በበኩላቸው "ላለፉት ስድስት ዓመታት ሩብ ሄክታር መሬቴን ጫት እያለማሁ ቆይቻለሁ" ብለዋል፡፡

"ዘንድሮ የጫት ተክሌን መንጥሬ በማስወገድ ለአቦካዶና ለማንጎ መትከያ የሚውል ጉድጓድ በመቆፈር ግብርና ጽህፈት ቤት የሚያቀርብልኝን ችግኝ እየተጠባበኩ እገኛለሁ" ስሉ ገልጸዋል፡፡

"ጫት ለጤና ጎጂ መሆኑን ባገኘሁት ስልጠና ተገንዝቤ ግማሽ ሄክታር የጫት መሬቴ ላይ በመስኖ በመታገዝ ሰብል ለማልማት ተዘጋጅቻለሁ" ያለው ደግሞ በወረዳው የሶር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሊ በእውቀት ነው፡፡

ጫት በማልማት የሚገኘውን ገቢ ፍራፍሬ በማልማት እንደሚያገኘው በመተማመን ወደ መስኖና ቋሚ ተክሎች ልማት ሥራ ውስጥ መግባቱን ገልጾ፣ ትውልድ ገዳይ የሆነውን የጫት ልማት ለማቆም መወሰኑን ተናግሯል።

አርሶ አደሮቹ ጫትን በማስወገድ ለምንጀምረው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በቂ የችግኝ አቅርቦት እንዲመቻችላቸውም ጠይቀዋል፡፡

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባይለየኝ አድማሱ በወረዳው 8 ቀበሌዎች የሚገኙ ከ70 በላይ አርሶአደሮች በጫት ልማት ተሰማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከአርሶ አደሩ ጋር በተደረገ ውይይት ሁሉም አርሶአደሮች የጫት ተክል የሚያደርሰውን ማህበራዊ ቀውስና የጤና ችግሮች በመገንዘብ የጫት መሬታቸውን በአትክልትና ፍራፍሬ ለመተካት የጋራ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ግብርና ጽህፈት ቤቱ የጫት መሬታቸውን በምግብ ሰብሎችና በሌሎች የገቢ ማስገኛ የፍራፍሬ ተክሎች ለመተካት ለተዘጋጁ አርሶአደሮች ከ60 ሺህ በላይ የማንጎና የአቦካዶ ችግኞች የማሰራጨት ሥራ ጀምሯል፡፡

በዚህ ዓመት በወረዳው 20 ሄክታር የጫት መሬት በሌሎች ሰብሎች ለመተካት መታቀዱንም ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው ፈጻጸም 12 ሄክታር የጫት መሬት ሰብልን ጨምሮ በአትክልትና ፍራፍሬ የመተካት ሥራ በአርሶ አደሩ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም