ቀጥታ፡

የኤርትራ የባህል ቡድን የሁለቱ ህዝቦች የመራራቅ ዘመን ዳግም እንደማይመለስ ማሳያ ነው.... አምባሳደር አርአያ ደስታ

ባህር ዳር የካቲት 10/20 " ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኤርትራ የባህል ቡድን የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች የመራራቅ ዘመን ዳግም እንደማይመለስ ማሳያ ነው " ሲሉ በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር አርአያ ደስታ ገለጹ።

63 የልኡካን ቡድን አበላትን የያዘው የኤርትራ የባህል ቡድን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት የሚያሳይ የሙዚቃ ትርኢት በባህር ዳር ከተማ አቅርቧል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት አምባሳደር አርአያ ደስታ በአስተርጓሚያቸው በኩል እንደገለጹት የባህል ቡድኑ አንጋፋና ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማካተት ባህር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ኪነ-ጥበብን ተጠቅሞ መልዕክት ያስተላልፋል።

"የባህል ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በደም የተሳሰሩ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ላለፉት 20 ዓመታት የገቡበት ቅራኔ ዳግም የማይመለስና ያበቃለት ስለመሆኑ በተግባር  የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

አምባሳደር አርአያ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በህዝቦች መካከል ሳይሆን በመሪዎች መካከል ተፈጥሮ በነበረ አለመግባባት ሁለቱ በደም የተሳሰሩ ህዝቦች ለዓመታት ተለያይተው ቆይተዋል።

“ህዝቦች ሰላማቸው እንዲጠበቅና በፊት የነበራቸው ግንኙነት እንዲመለስ የነበራቸው ትግልና ፍላጎት በበሳል አመራር ታግዞ በአሁኑ ወቅት እውን ሊሆን ችሏል ። ”

ከዚህ በኋላ ሁለቱን ህዝቦች ሊነጣጥላቸው የሚችል ማንም አካል ተቀባይነት አያገኝም፤ የባህል ቡድኑ ኪነጥበባዊ ጉብኝትም የእዚህ ዋና ማሳያ ነው” ብለዋል።

 “ጦርነት ሰልችቶናል ከወንድሞቻችን ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደ ቀደመው  አብሮ በሰላም ለመኖር የነበረን ምኞት እውን በመሆኑ ተደስተናል” ያለው ደግሞ “ሳባ ሳቢ ናይን” በሚል ዘፈኑ የሚታወቀው አንጋፋው አርቲስት ኢንጂነር አስገዶም ወልደሚካኤል ነው።

ኤርትራዊያን አርቲስቶች ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ሁሉ ሁለቱን አገራት አንድ የሚያደርግ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግሯል።

“የሥራችን ውጤት ፍሬ አፍርቶና በበሳል አመራሮች ታግዞ ሁለቱ ህዝቦች በአዲስ መንፈስ መቀራረብ ጀምረዋል ያለው አርቲስት አስገዶም” ግንኙነቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና ለህዝቦች ተጠቃሚነት ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግሯል።

 “የአማራ ህዝብ ላለፉት 20 ዓመታት ከኤርትራውያን ወገኑ ጋር መነጠሉ ሰላሙን ነስቶት ቆይቷል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌው ናቸው።

በደም የተገመደን ህዝብ መሪዎች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ነጣጥለውት ቢቆዩም ህዝብ ይሁንታ ስላልሰጠው እንዲለያዩ የተገደዱ ህዝቦች ዳግም በራሳቸው ጥረትና በአስተዋይ መሪዎች እገዛ ጭምር ሊገናኙ መቻላቸውን ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅትም የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት በተለይ የአማራና የኤርትራን ህዝብ  መልካም ግንኙነት የማይሹ ጸረ-ሰላም ኃይሎች በመኖራቸው ህዝቡ በጥንቃቄና በአስተውሎ ሊመለከተው ይገባል” ብለዋል።

የአማራ ህዝብ ለኤርትራዊያን እህትና ወንድሞቹ ያለው ጥልቅ ፍቅር በቃል ከሚገለጽ በላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ላቀ፣ ለእዚህም ህብረተሰቡ ከ20 ዓመት በፊት በአደራ የተቀበለውን ቤትና ንብረት በአሁኑ ወቅት ማስረከብ መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የሁለቱ አገራት ህዝቦች በደም የተሳሰሩ እንደመሆናቸው መጠን በተራ አሉባልታ መለያየት እንደማይቻል ያስረዱት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የተጀመረው ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሥራቸውን አጠናክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን ታሪካዊ ግንኙነት ለመጠናከርወደኢትዮጵያ የመጣው የባህል ቡድን በቀጣዮቹ ቀናት ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቱን በአዳማ፣ ሃዋሳና አዲስ አበባ እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም