ቀጥታ፡

ልዩነቶችን በማቻቻል ለሀገር ፍቅርና አንድነት መታገልን ከአድዋ ጀግኖች እንማር---የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

አክሱም የካቲት 9/2011 ጀግኖች አባታቻችን ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በማቻቻል ለሀገር ፍቅርና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው አድዋ ላይ ከፈጸሙት ገድል ትምህርት መውሰድ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

"አባቶች የሀገር ሉአላዊነትንና ነጻነትን በማስቀደም ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር አድዋ  ላይ ድል በማድረግ የፈጸሙት ጀግንነት ኢትዮጵያን በአለም ተጠቃሽ አድርጓታል" ብለዋል።

አድዋ ላይ የተፈጸመው ጀግንነትና የነጻነት ተምሳሌት ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠውም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ገብረህይወት ሃይለማርያም እንደገለጹት ስለ ሀገር ፍቅር፣ ነጻነት እና አንድነት ከአድዋ ድል መማር ይገባል።

"ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሆን በወራሪው የጣልያን ላይ ያገኙት ድል የአፍሪካውያን እና የአለም ጥቁር ህዝቦች የአንድነትና ነጻነት ተምሳሌት ነው" ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ ከጀግኖች አያቶች እና ከአርበኞች ስለ ሀገር ፍቅር፣አንድነት እና ጀግንነት ብዙ መማር እንደሚገባውም አስረድተዋል።

"የሀገር ሉአላዊነትን ለማሰከበር እና የውጭ ወራሪን ለመከላከል ኢትዮጵያውያን በአንድነት የተጎናጸፉት የአድዋ ድል የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ድል ነው"  ብለዋል፡፡

"ጀግኖች አባቶች ለነጻነትና ለሉአላዊነት የህይወት መስዋእትነት የከፈሉት የሀገር ፍቅር እና አንድነት ስለነበራቸው ነው" ያሉት ምሁሩ "የአሁኑ  ትውልድ የፖለቲካ ልዩነቶቹን በማቻቻል የሀገር ፍቅር እና አንድነትን ለማጠናከር ቅድሚያ መስጠትን ከአድዋ ድል መማር አለበት" ብለዋል።

መምህር ገብረህይወት አያይዘውም "ከጀግኖች አባቶች የተረከብናትን ሀገር ማልማትና እና ሰላሟን መጠበቅ ግዴታችን ነው" ብለዋል፡፡

"የዓድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፈጠርና ለአፍሪካ አንድነት መመሰረት መሰረት የጣለ  ነው"ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ገብረመድህን መዝገበ  ናቸው፡፡

"በቅድመ አያቶቻችንን ደምና አጥንት የተጻፈ ደማቅ የድል ታሪክ ተገቢው ትኩረት አገኝቷል ለማለት አያስደፍርም" ያሉት መምህሩ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአድዋ ከፈጸሙት አኩሪ ድል ትውልዱ መማር እንዳለበት ተናግረዋል።

በአድዋ ድል አያቶቻችን ያከናወኑት ገድል ለሀገራችን ህዝቦችና ለመላው አለም ጥቁር ህዝቦች ታሪካዊነቱን ጠብቆ ለትውልድ አንዲተላለፍ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህን ተግባራዊ የሚያደርግ ተቋም ሊኖር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ግንባታን ለማጠናከር የኢትዮጵያ መንግስት ሃላፊነት ወስዶ አፍሪካውያንን ማንቀሳቀስ እንዳለበትም ምሁሩ ተናግረዋል፡፡

"የአድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም መነሻ ነው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ደግሞ ለአፍሪካ አንድነት መመሰረት አስተዋጽኦ አለው" ብለዋል።

አፍሪካውያን አህጉራዊ ትስስር ፈጥረው ወደ አንድትና ህብረት እንዲመጡ የአፍሪካውያንን ልእልና ለማሳደግ የአድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረም አቶ ገብረመድህን ጠቁመዋል።

"አፍሪካውያን ያካሄዷቸውን የነጻነት ተጋድሎ እንቅስቃሴዎች የሚዘከርበት ዘመናዊ ማእከል ሆኖ እንዲያገለግል ለዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም