ቀጥታ፡

በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ግብረ ኃይል ተቋቋመ

ጎንደር የካቲት 9/2011የማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው ትናንት በሰጡት መግለጫ ተፈናቃዮቹን በሁለት ወራት  ውስጥ ወደ ቀያቸው በመመለስ ሥራው የተጀመረው ግብረ ኃይል በማቋቋም ነው።

በዚህም በጭልጋና አካባቢው በተፈጠረ ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 50ሺህ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸውን ለማቋቋም ከክልል እስከ ወረዳ ደረጃ ባለው መዋቅር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ግብረ ኃይሉ በጭልጋ ፣ በላይ አርማጭሆ ፣ በምዕራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች መኖሪያ ቤታቸው የተቃጠለባቸውን 3ሺህ አባወራዎች መኖሪያ ቤት ለመገንባት በጥናት ለይቷል ብለዋል፡፡

ለእያንዳንዱ አባወራ 59 የቤት ክዳን ቆርቆሮ እንደሚሰጥ አቶ መንበሩ አስታውቀዋል።

ጎንደር ዩንቨርሲቲና ጅግዳን የተባለ ኮሌጅ ለቤት ክዳን ቆርቆሮ መግዣ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብ የቤት መስሪያ እንጨት ለመለገስ ቃል ገብቷል።

በግጭቱ የተፈናቀሉት በአብዛኛው አርሶ አደሮች እንደመሆናቸው በአጭር ጊዜ ወደ ግብርና ሥራ ለማስገባት ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና የእርሻ መሣሪያዎች የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸላቸው ነው፡፡

ተፈናቃዮቹ በጊዜያዊ መጠለያ ከገቡ ጀምሮ መንግሥትና አጋር አካላት ከዕለት እርዳታ ጀምሮ ነጻ የሕክምና አገልግሎትና የቤት መገልገያ ቁሳቁስ በማቅረብ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡

በአይምባ ጊዚያዊ መጠለያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አባ ምህረቴ ሞላ በጊዜያዊ መጠለያው ሰብዓዊ እርዳታው ያልተጓደለባቸው ቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ሞሚና ሰይድ የተባሉ ተፈናቃይ በበኩላቸው አካባቢው ወደ መረጋጋት እየተመለሰ በመሆኑ ወደ ቀያችን ተመልሰው መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም