የጋሞና የጎፋ ዞኖች በጋራ መልማት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለማጠናከር ይሰራሉ - ዋና አስተዳዳሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጋሞና የጎፋ ዞኖች በጋራ መልማት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለማጠናከር ይሰራሉ - ዋና አስተዳዳሪዎች
ሶዶ የካቲት 9/2011 የሕዝቦችን የጋራ ዕሴት ግንባታ በማስቀደም በጋራ መልማት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩ የጋሞና የጎፋ ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች ገለጹ፡፡
የዞኖቹ ዋና አስተዳዳሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የዞን መዋቅር የተፈጠረው ለመንግሥታዊ አገልግሎት ቅርበት እንጂ ለልዩነት አይደለም።
አዲስ የተመሰረተውን የጎፋ ዞን በምክትል ዋና አስተዳዳሪነት እንዲመሩ የተሾሙት ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ የተሳለጠ የመንግሥት አገልግሎት በቅርበት ለማግኘት የአካባቢው ሕዝብ የመዋቅር ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የጥያቄው ምላሽ ማግኘት በአካባቢው ያሉ ጸጋዎችና ምቹ አጋጣሚዎችን አሟጦ ለመጠቀም እንደሚያስችልና የሕዝብን የመልማት ጥያቄ እንደሚፈታ ተናግረዋል።
ከጋሞ ዞን ሕዝቦች ጋር ያሉ የጋራ ዕሴቶች ግንባታ ላይ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ አንድነት ለመፍጠር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ፣ ግብርናውን ማዘመን ፣ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራና ለመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ሥራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃርኮ ደምሴ በበኩላቸው ለመንግሥታዊ አገልግሎት እንዲያመችና በቅርበት ሕዝብን ለማገልገል በሚል አዲስ መዋቅር ቢፈጠርም፤ የወንድማማች ሕዝቦችን የጋራ ዕሴት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ግጭትን የመፍታትና ሰላምን የማጎልበት ልዩ ባህል ለማሳደግ ለአገራዊ ሰላም መስፈን በጋራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
የሁለቱንም ዞኖች ሕዝቦች በጋራ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲጠቀሙ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጰያ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ንቅናቄ/ደኢህዴን/ና ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ የዞኖቹ የመዋቅር ጥያቄ በጥናት መመለሱን ይናገራሉ።
በዚህም የሁለቱን ሕዝቦች የመልማት ፍላጎት ለመመለስ በመሠረተ ልማት ማስተሳሰርን ጨምሮ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በጋራ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጎፋ ዞን ነዋሪው አቶ ዕድገቱ እስራኤል የአካባቢው ሕዝብ ጥያቄ በወቅቱ ፈጣን ምላሽ ሳያገኝ በመቆየቱ በህዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ ፈጥሮ መቆየቱ ጠቁመው አሁን "ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያለውን ሰላም በማጠናከር በጋራ ለመልማት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።
በደቡብ ክልል መንግሥት በተደረገ ጥናት ጎፋ በዞን ደረጃ እንዲዋቀር የተደረገው በቅርቡ ነው፡፡