የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላት ምዝገባ የካቲት 30 ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላት ምዝገባ የካቲት 30 ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ የካቲት 9/2011 በተያዘው በጀት አመት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላትና ተጠቃሚዎች ምዝገባ የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ገለፀ።
በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀሪዎቹ ጊዜያት እንዲመዘገቡም ኤጀንሲው ጥሪ አስተላልፏል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ጤና አገልግሎት አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ የጤና ችግር ሲያጋጥም ያለክፍያ የጤና አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ነው።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚዛን ኪሮስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በዚህ ዓመት አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 522 ወረዳዎች በተጨማሪ በ159 ወረዳዎች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል።
ወረዳዎቹ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን የሚተገበርባቸው ወረዳዎች አጠቃላይ ቁጥር 681 የሚደርስ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ከ18 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ኪሮስ ወረዳዎቹ ስርዓቱን ተግባራዊ ሲያደርጉ የተጠቃሚው ቁጥር 20 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል አመልክተዋል።
የጤና መድህን ስርዓት ለአገሪቱ አዲስ በመሆኑ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ 36 በሚደርሱ የተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በመጠቀም በመገናኛ ብዙሃን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የጤና መድህን ተጠቃሚዎች የሚያነሱትን ቅሬታ ለመፍታት በዚህ ዓመት በተለየ ትኩረት እንደሚሰራመም ተናግረዋል።
ከመድሃኒት እጥረትና ከላቦራቶሪ አገልግሎት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ኤጀንሲው መድሃኒትና አገልግሎቶችን በፓኬጅ ለመግዛት የሚያስችለውን ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሚዲያዎች ስለ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን በተመለከት የጀመሯቸውን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች ነበር ፤ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ከማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን በተጨማሪ በደመወዝ የሚተዳደረውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያቅፍ ማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት ለመጀመር በ2002 ዓ.ም አዋጅ የወጣ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም።