ቀጥታ፡

ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ ጽዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ የፎረሙ ተሳታፊ ከተሞች ሊሰሩ ይገባል

ጂግጂጋ የካቲት 9/2011 ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ ፣ ጽዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ የከተሞች ፎረም ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስገነዘበ።

8ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም 'መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልፅግና' በሚል መሪ ሃሳብ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ነው።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽ ሚኒስትሩ አቶ ዣንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት  የከተሞችን እድገት ለማቀራረብና ተሞክሮ መለዋወጫ መድረክ ለመፍጠር የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም ተፈጥሯል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደት በጠራ ፕላን የሚመሩ ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥሩ የኢንዱስትሪ ማዕከል የሚሆኑ ከተሞች ለመፍጠር መስራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

ከተሞች ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር የሚተገበርባቸው ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ ፅዱና በአረጓዴነት የተሞሉ እንዲሆኑ ተሳታፊ ከተሞች የቤት ስራውን በአፅንኦት ወስደው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ ፎረሙ ከተሞች እርስ በእርስ የመደጋገፍ፣ በጋራ የመስራትና የማደግ ባህል ለማስፋትና በመነጋገር አዳዲስ ሃሳቦች ለማመንጨት ታስቦ መጀመሩን ተናግረዋል፡

''ከተሞች የዲሞክራሲ እና አብሮ የመኖር ተምሳሌት መገለጫ የብዙ ቀለማት ውጤት የምናይበት መሆን ይገባቸዋል'' ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ጅግጅጋ ከተማ ትልቅ ማሳያ እንደምትሆን ተናግረዋል።

''የዘንድሮው በዓልም ለከተሞቻችን እድገት ተጨማሪ ትልቅ ኃላፊነት ለመወጣት የላቀ ርብርብ የምናደርግበት ወቅት ነው'' ብለዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታና የፎረሙ አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው ''እስካሁን የተካሄዱ የከተሞች ፎረም የከተሞችን ትውውቅ በማሳደግ በጎ ገፅታን መፍጠር ችሏል'' ብለዋል።

ከዚህም ሌላ ፎረሙ የስራ ፈጠራ እንዲበረታታ ከማድረጉ በተጨማሪ ጤናማ የሆነ የከተሞች የልማትና የስራ ውድድር በመካከላቸው እንዲፈጠር ማስቻሉንም ገልፀዋል።

ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች የማስተዋወቂያ መድረክ ሆኖ መዝለቁንም ነው ያስታወቁት።

የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ጅግጅጋ ከተማን በተለይ ባለፉት አምስት ወራት መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ለማድረግ ትልቅ ስራ የተሰራበት እንደሆነ ገልፀዋል።

የክልሉ መንግሥት የሥራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት ሥልጠና በመስጠት፣ የመሸጫና የማምረቻ ቦታዎች በመገንባት የብድር አገልግሎት በማቅረብ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ትኩረት በመስጠት ክልሉ በዘንድሮ በጀት ዓመት የ2ሺህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።፡

የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የከተማዋን ችግር ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጥረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በዓሉ በጅግጅጋ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በፓናል ውይይቶችና በኤግዝቢሽኖች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም