በቄለም ወለጋ ዞን 235 ትምህርት ቤቶች ሥራ ጀመሩ

77

ነቀምቴ የካቲት 9/2011 በቄለም ወለጋ ዞን በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 235 ትምህርት ቤቶች ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራሞች የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዲሪባ ሺፈራው እንደገለጹት ትምህርት ቤቶቹ ሥራ የጀመሩት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች አንፃራዊ ሰላም በመፈጠሩ ነው ።

አንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች   በተቆራረጠ መንገድ ትምህርት ሲሰጥባቸውና ሙሉ ለሙሉ ትምህርት አቋርጠው የነበሩ 81 ትምህርት ቤቶች ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸው የተመለሱት እስከ የካቲት 4 ቀን 2011 በነበረው ጊዜ ውስጥ ነው ።

የማሎጊ ወለል ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ኢርኪሣ በሰጡት አስተያየት በወረዳቸው የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ስራቸው ከተመለሱ አንድ ሳምንት ሞልቷቸዋል።

በወረዳው ገተማ ኦሊቃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዳዊት ኃይሉ በሰጡት አስተያየት የመማር ማስተማር ሥራውን በፀጥታ ችግር ምክንያት አቋርጦ የነበረውን ትምህርት ቤታቸው ወደ መደበኛ ሥራው መመለሱን ገልጸዋል።

በችግሩ ሳቢያ የተስተጓጎለውን ትምህርት በማካካስ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የአንደኛ መንፈቀ ዓመት ፈተና ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ።

የተጆ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደበላ መርጋ በበኩላቸው ትምህርት ቤታቸው ከጥር 27 ቀን2011 ዓ.ም ጀምሮ  ወደ መደበኛ ሥራው ተመልሷል።

የግዳሚ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ በፍቃዱ በወረዳቸው መደበኛ ሥራቸውን አቋርጠው የነበሩ 50 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም